በተስፋለም ወልደየስ
በኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ እና በክልል ደረጃ የሚንቀሳቀሱ 17 የጋዜጠኞች ማህበራት፤ የጋዜጠኞች የደህንነት ጥምረትን ለመመስረት የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ። ዛሬ አርብ ግንቦት 26፤ 2014 መመስረቱ ይፋ የተደረገው የማህበራት ጥምረቱ ዋነኛ ዓላማው “የጋዜጠኞችን ደህንነት ማስጠበቅ መሆኑ” ተገልጿል።
የመግባቢያ ስምምነት ሰነዱን ከተፈራረሙት ውስጥ የትግራይ፣ የአማራ፣ የኦሮሚያ እና የደቡብ ክልል የጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበራት ይገኙበታል። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር፣ የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማህበር እና የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበርም ከፈራሚዎቹ ዝርዝር ውስጥ ተካትተዋል።
“እነዚህ ማህበራት የጋዜጠኞችን ደህንነት ለማስጠበቅ ከዚህ ቀደም በተናጠል የሚሰሩት ስራ እንዳለ ሆኖ ከዚህ በኋላ በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል” ሲሉ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበርን ወክለው በዛሬው የጥምረት መመስረቻ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የማህበሩ ስራ አስፈጻሚ አባል እታገኘሁ መኮንን ተናግረዋል። “በዋነኛነት ይህ ጥምረት ለጋዜጠኛው የህግ እና ተያያዥ የሆኑ ሌሎች ድጋፎችን የማድረግ የደህንነት ስራዎችን የመስራት ስራ ላይ አጥብቆ የሚሰራ ነው” ሲሉም አክለዋል።
በአስራ ሰባት ማህበራት የተመሰረተው ጥምረት፤ ለችግር የተጋለጡ፣ የደህንነት ስጋት ያለባቸው፣ ተገቢ ያልሆነ እስር እና እንግልት እየደረሰባቸው ላሉ ጋዜጠኞች የህግ እና ሌሎችም ድጋፎች እንደሚያደርግ በዛሬው መርሃ ግብር ላይ ተነግሯል። ጥምረቱ ጋዜጠኞች ከለላ በሚያስፈልጋቸው ጊዜያቶች ሁሉ ከጎናቸው ይቆማልም ተብሏል።
የማህበራት ጥምረቱ፤ በጋዜጠኞች ደህንነት ዙሪያ ህጎች እንዲወጡ፣ ከጋዜጠኝነት ሙያ ስራ ጋር በተያያዘ የወጡ ሃገር አቀፍ ህጎች ተግባር ላይ እንዲውሉ፣ መስተካከል የሚገባቸው ህጎች እንዲሻሻሉ እንዲሁም የጋዜጠኝነት የስነ ምግባር መርሆዎች እንዲከበሩ እንደሚሰራ የመስራች ማህበራቱ ተወካዮች አስታውቀዋል። ጥምረቱ፤ ጋዜጠኞች የህግ ድጋፍ፣ ጥበቃ እና የህግ ከለላ በተገቢው መንገድ እንዲያገኙ የማድረግ ስራን እንደሚያከናውንም ገልጸዋል።

በመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ደህንነት ላይ ትኩረቱን ያደረገው የማህበራት ጥምረቱ፤ ጋዜጠኞች በተለያየ አካባቢ ለዘገባ ሲንቀሳቀሱ ሊያጋጥማቸው የሚችሉ የስጋት ቀጠናዎችን በመለየት ቀድመው እንዲያውቋቸው የማድረግ እቅድ እንዳለው በዛሬው መርሃ ግብር ላይ ተነስቷል። ጥምረቱ፤ ለጋዜጠኞች የደህንነት እና የቅድመ ጥንቃቄዎች መመሪያዎች የማውጣት እቅድ እንዳለውም ተጠቁሟል።
በጋዜጠኛ ሙያ ማህበራት መካከል የእርስ በእርስ መደጋገፍ እንዲኖር እንደሚሰራ የተነገረለት ጥምረቱ፤ ከህግ አካላት፣ ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና ከሌሎች ማህበራት ጋር በመተባበር ለመስራት ማቀዱ ተመላክቷል። ጥምረቱን ለመመስረት በዛሬው መርሃ ግብር ፊርማቸውን ያኖሩት የ17 የማህበራት ተወካዮች፤ ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ሙያ ማህበራትም ጥምረቱን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አስተላልፈዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)