በአምስት ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ባለቤቶች ጉዳይ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ለነገ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

በሃሚድ አወል

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአምስት ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ባለቤቶችን ጉዳይ መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለነገ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ። ለነገ ማክሰኞ ግንቦት 30፤ 2014 ቀጠሮ የተሰጣቸው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ተመስገን ደሳለኝ፣ ያየሰው ሽመልስ፣ መዓዛ መሐመድ፣ መስከረም አበራ እና ሰለሞን ሹምዬ ናቸው።

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ተለዋጭ ቀጠሮውን ከመስጠቱ በፊት መርማሪ ፖሊስ በተፈቀደለት የምርመራ ጊዜ አከናውኛችኋለሁ ያላቸውን ዝርዝር ተግባራት አቅርቧል። በፖሊስ ማብራሪያ ላይ በመንተራስ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹን የወከሉ ጠበቆች ያቀረቡትን መከራከሪያዎች እና የዋስትና ጥያቄዎችንም ፍርድ ቤቱ አድምጧል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አምስቱንም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች “ሁከት እና ብጥብጥብ በማነሳሳት ወንጀል” እንደጠረጠራቸው ከዚህ ቀደም በነበራቸው የፍርድ ቤት ውሎ ቢገልጽም፤ የተጠርጣሪዎቹ ጉዳይ ዛሬ ችሎት ፊት የቀረበው ግን በተለያየ መዝገብ ነው። በችሎቱ በቅድሚያ የታየው፤ “ኢትዮ ንቃት” የተሰኘ የዮቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነችው የመስከረም አበራን የምርመራ ጉዳይ ነው።

የመስከረምን ጉዳይ የያዘው መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በነበረው የችሎት ውሎ በተፈቀደለት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ያከናወናቸውን ተግባራት ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ግንቦት 16፤ 2014 በነበረው የችሎት ውሎው፤ ፖሊስ በተጠርጣሪዋ ላይ እያካሄደ ያለው ምርመራ “ጅምር ስለሆነ እና ብዙ የሚሰሩ ስራዎች” የሚቀሩ መሆናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት 13 የምርመራ ቀናት ፈቅዶ ነበር።  

ፖሊስ በእነዚህ የምርመራ ቀናት፤ ሐዋሳ በሚገኘው የተጠርጣሪዋ መኖሪያ ቤት ብርበራ ማካሄዱን ዛሬ ሰኞ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል። በብርበራውም በእጅ የተጻፉ፣ ሁከት እና ብጥብጥ የሚያነሳሱ ጽሁፎች እንደዚሁም የውጭ ሀገር ገንዘቦች ማግኘቱን ለችሎቱ አስረድቷል። ከዚህ በተጨማሪም የተጠርጣሪዋን የገንዘብ ዝውውር ለማወቅም ለ18 ባንኮች ደብዳቤ መጻፉን አስታውቋል።

ፖሊስ በዚሁ ማብራሪያው፤ መስከረም አበራ የመገናኛ ብዙሃን ባለቤት መሆኗን ለፍርድ ቤቱ ገልጿል። የመገናኛ ብዙሃኑን መጠሪያ በስም ያልጠቀሰው መርማሪ ፖሊስ፤ የሚዲያውን ህጋዊነት ለማረጋገጥ ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ደብዳቤ ጽፎ ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑንም አስታውቋል። ይህን ደብዳቤ ጨምሮ ለሌሎች ተቋማት የጻፋቸውን ደብዳቤዎች ምላሽ ለመጠባበቅ እንደዚሁም ከተጠርጣሪዋ መኖሪያ ቤት የተገኙ የሰነድ እና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ለማስመርመር፤ ፖሊስ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ችሎቱን ጠይቋል።

ዛሬ ለሶስተኛ ጊዜ ችሎት ፊት የቀረበችውን መስከረም አበራን የወከሉት ሶስት ጠበቆች፤ የፖሊስን  የተጨማሪ የምርመራ ቀናት ጥያቄ ተቃውመዋል። ከመስከረም ጠበቆች አንዱ የሆኑት አቶ ሔኖክ አክሊሉ፤ ደንበኛቸው በምርመራ ወቅት ሲቀርብላት የነበረው ጥያቄ ከተጠረጠረችበት ወንጀል ጋር ያልተያያዘ እንደነበር በተጨማሪነት ለችሎቱ ገልጸዋል። 

“ጄነራል አበባው ታደሰን፤ ፊልድ ማርሻሉን በጽሁፎችሽ አሳቅቀሻል። ከፍተኛ የጦር ጄነራሎችንም አሳቅቀሻል የሚል ጥያቄ ነበር ሲቀርብላት የነበረው” ያሉት ጠበቃው፤ “በእሷ ጽሁፍ ተሳቀቅኩ” የሚል ሰው በሌለበት በዚህ ልትጠየቅ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል። ለጠበቃው መከራከሪያ ምላሽ የሰጡት መርማሪ ፖሊስ፤ ተጠርጣሪዋ “ ‘[የጄነራል] ሰዓረን ዕጣ ፈንታ ይገጥመዋል’ የሚል ጽሁፍ ጽፋ ነበር። ጉዳዩ ስለግለሰብ አይደለም። ሀገር ላይ ስለሚያስከትለው ነገርም ነው” ብለዋል።

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በተከታይነት የተመለከተው፤ “ሮሃ ሚዲያ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት መዓዛ መሐመድን መዝገብ ነው። ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ችሎት ፊት የቀረበችው መዓዛ፤ ከጓደኛዋ መኖሪያ ቤት በፖሊስ የተያዘችው ከዘጠኝ ቀናት በፊት ግንቦት 20፤ 2014 ነበር። 

መዓዛን ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረበችው የዛሬ ሳምንት ሰኞ ግንቦት 22 ነው። በተጠርጣሪዋ ላይ እየተካሄደ ያለው ምርመራ ጅምር በመሆኑ እና ጋዜጠኛዋ “የገንዘብ ድጋፍ ታገኛለች” በሚል በፖሊስ የቀረበው ምክንያት ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግበት በሚል፤ ፍርድ ቤቱ ሰባት የምርመራ ቀናት ፈቅዶ ነበር።

መርማሪ ፖሊስ በዛሬው የችሎት ውሎ፤ በተሰጡት የምርመራ ቀናት በጋዜጠኛዋ መኖሪያ ቤት በብርበራ የተገኙ “ሁከት ቀስቃሽ” ጽሁፎችን ለብሔራዊ ደህንነት እና “ለተለያዩ አካላት” መላኩን ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም፤ የተጠርጣሪዋን የገንዘብ ዝውውር ለማወቅ ለባንኮች ደብዳቤ መጻፉን እንደዚሁም ሁከት እና ብጥብጥ ቀስቃሽ የሆኑ ንግግሮችን ከበይነ መረብ በ“ማውረድ” በምርመራ መዝገቡ ማያያዙን አብራርቷል። 

“ግጭት ቀስቃሽ ጽሑፎች ላይ በባለሙያ ትንታኔ ለማስደረግ” እና ለተቋማት ለተላኩ ደብዳቤዎች ምላሽ ለመጠባበቅ ፖሊስ ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናትን በመዓዛ ላይ ጠይቋል። ጋዜጠኛዋን ወክለው በችሎት የተገኙት ሁለት ጠበቆች ፖሊስ ያቀረባቸው ምክንያቶች ለጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ በቂ አይደሉም ሲሉ ተቃውመዋል። ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ “ፖሊስ ሁሉንም ነገር አጠናቅቋል” ሲሉ ችሎቱ የደንበኛቸውን የዋስትና መብት እንዲያከብር ጠይቀዋል።

የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ በሶስተኛነት የተመለከተው የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ጉዳይ ነው። የ“ፍትሕ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆነው ተመስገን፤ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ከ11 ቀናት በፊት ግንቦት 18፤ 2014 ነበር። የጋዜጠኛውን ጉዳይ የሚመለከተው ችሎቱ፤ በጋዜጠኛው ላይ የ10 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቅዶ ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።

መርማሪ ፖሊስ ባለፉት 10 ቀናት የጋዜጠኛውን የገንዘብ ዝውውር ለማወቅ ለባንኮች ደብዳቤ መጻፉን ገልጿል። ጋዜጠኛው “አመጽ እንዲነሳሳ” አስተላልፏቸዋል ያላቸውን መልዕክቶችም ለብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት መላኩንም አስታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ የ“ፍትሕ” መጽሔትን ከሚያሳትመው “ኢትዮ ከለር አታሚዎች” 105 የ“ፍትህ” መጽሔት ዕትሞችን በመውሰድ ምርመራ እየተከናወነ መሆኑንም ፖሊስ ጠቅሷል።

ፖሊስ ምርመራውን ጨርሶ ለማከናወን፣ የምስክሮችን ቃል ለመቀበል እና ለጻፋቸው ደብዳቤዎች ምላሽ ለመጠባበቅ ፍርድ ቤቱ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቅድለት ጥያቄ አቅርቧል። የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጠበቃ አቶ ሔኖክ አክሊሉ፤ በመርማሪ ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ላይ አስተያየት ከመስጠታቸው በፊት በደንበኛቸው አያያዝ እና የሰብዓዊ መብት አጠባበቅን የተመለከተ ረዘም ያለ አቤቱታ አቅርበዋል። 

አቶ ሔኖክ ከዚህ በፊት በነበረው ችሎት ከተመስገን የእስር ቤት አያያዝ ጋር በተያያዘ ያቀረቡት አቤቱታ አለመሻሻሉን እና “ተባብሶ መቀጠሉን” ለችሎቱ አስረድተዋል። በጉዳዩ ላይ የእስረኞች አስተዳደር ኃላፊ ችሎት ቀርበው እንዲያብራሩ ትዕዛዝ እንዲሰጥም ጠይቀዋል።

“ደንበኛዬ ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው ነው” ያሉት አቶ ሔኖክ፤ ጋዜጠኛ ተመስገን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ድብደባ እንደተፈጸመባቸውም ለችሎቱ ገልጸዋል። ደንበኛቸው ድብደባውን ተከትሎ ላጋጠማቸው የጤና እክል ህክምና መከልከላቸውንም አክለዋል። በችሎቱ ንግግር ያደረገው ጋዜጠኛ ተመስገንም “ግልጽ የሆነ ድብደባ ተፈጽሞብኛል” ሲል ክስተቱን ለችሎቱ አረጋግጧል። 

ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የመጡት መርማሪዎች በበኩላቸው ደብደባ አለመፈጸሙን ገልጸው “ፍርድ ቤቱ የተቋም ስም እየጠፋ ስለሆነ ማሳሳቢያ ይስጥልን” ሲሉ አመልክተዋል። አቤቱታዎች አለመሻሻላቸውን በተመለከተም “የተቋማችን እስር ቤት እድሳት ላይ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የፖሊስን የምርመራ ጊዜ ጥያቄ በተመለከተ ጠበቃ ሔኖክ ባቀረቡት መከራከሪያ “ጋዜጠኛ ተመስገን ሲያዝ ፖሊስ ወንጀል ስለመፈጸሙ መረጃ ሳይኖረው ነው” ብለዋል። አቶ ሔኖክ “በምርመራው ‘ወንጀል እመን እና ውጣ ነው’ እየተባለ ያለው” በማለት አክለዋል። ጠበቃው፤ መርማሪ ፖሊስ ለተጨማሪ ጊዜ መጠየቂያ ያቀረባቸው ምክንያቶች ተመስገንን በእስር ለማቆየት በቂ አይደሉም ሲሉም ተሟግተዋል።

ጠበቃ ሄኖክ ከዚህ ቀደም በነበረው ችሎት መርማሪ ፖሊስ ጋዜጠኛ ተመስገንን በተመለከተ ያቀረበውን ውንጀላ በማስታወስ በድጋሚ ምላሽ ሰጥተዋል። ጋዜጠኛ ተመስገን ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት መርማሪ ፖሊስ፤ ተጠርጣሪው “ሁከት እና ብጥብጥ የሚያነሳሱ ቃለ ምልልሶችን በዩቲዩብ ሰጥቷል” ሲል ወንጅሎ ነበር። 

የተመስገን ጠበቃ፤ ጋዜጠኛው “ላለፉት አራት ዓመታት በየትኛውም የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን አልቀረበም” ሲሉ የፖሊስን ውንጀላ አስተባብለዋል። መርማሪ ፖሊስ ለዚህ መከራከሪያ በሰጠዉ ምላሽ “ወንጀሉ በማህበራዊ ሚዲያ ብቻ አይደለም [የተፈጸመው]። በ“ፍትህ” መጽሔት አሳትመው ባሰራጩት ጽሁፍም ነው” ሲል ተከራክሯል።

አቶ ሔኖክ ከዚህ በፊት በነበረው የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ላይ የ“ፍትህ” መጽሔት ጉዳይ አለመነሳቱን በማስታወስ “አዲስ ፍሬ ነገር ሊነሳ አይገባም” ሲሉ ለችሎቱ አመልክተዋል። ችሎቱ የፖሊስን ጥያቄ ውድቅ አድርጎ፤ ደንበኛቸው በዋስትና ወጥቶ ጉዳዩን ከውጭ ሁኖ እንዲከታተልም ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርበዋል። 

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአራተኛነት የተመለከተው ጉዳይ “ገበያኑ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነው የሰለሞን ሹምዬን ጉዳይ ነው። ሰለሞን እንደ ሌሎቹ ጋዜጠኞች ሁሉ “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል” የተጠረጠረ ሲሆን፤ በዛሬው ችሎት “የትም ቦታ መቼም ሁከት እና ብጥብጥ የሚያነሳሳ ንግግር አላደረግኩም” ሲል የቀረበበትን ውንጀላ ተቃውሟል። 

 ከ17 ቀናት በፊት ግንቦት 12 በፖሊስ የተያዘው ሰለሞን ዛሬ ፍርድ ቤት ሲቀርብ ለሶስተኛ ጊዜ ነው። የሰለሞንን ጉዳይ የያዘው መርማሪ ፖሊስ፤ ከዚህ ቀደም በነበረው ችሎት በፍርድ ቤት በተፈቀዱለት ሰባት የምርመራ ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት ዘርዝሯል። ፖሊስ በእነዚህ ቀናት፤ ሰለሞን ያደረጋቸውንን ንግግሮች ከበይነ መረብ ማውረዱን፣ ለባንኮች እና “ለተለያዩ መስሪያ ቤቶች” ደብዳቤ መጻፉን ለችሎቱ አስረድቷል።

ባለፈው ሳምንት ሰኞ በነበረው ቀጠሮ የተሰጡት ቀናት በቂ አለመሆናቸውን የገለጸው ፖሊስ፤ ግብረ አበሮችን ለመያዝ እና ምርመራውን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 14 ቀናት ችሎቱን ጠይቋል። የሰለሞን ሹምዬ ጠበቃ የሆኑት አቶ በፍቃዱ ስዩም፤ ግብረ አበር ለመያዝ ጋዜጠኛ ሰለሞን በእስር መቆየት የለባቸውም ሲሉ ተከራክረዋል። ደንበኛቸው “ሊጠየቁ የሚገባው በራሳቸው የወንጀል ድርጊት ነው” ሲሉ ተሟግተዋል። “ሻይ ቡና” በተሰኘው የቴሌቭዥን ፕሮግራሙ ይበልጡኑ የሚታወቀው ሰለሞን በበኩሉ፤ ችሎቱ የዋስትና መብቱን እንዲጠብቅለት ጥያቄ አቅርቧል። 

በዛሬው የችሎቱ ውሎ ጉዳዩ በመጨረሻ የታየለት ጋዜጠኛ የቀድሞው የ“ኢትዮ ፎረም” የዩቲዩብ መገናኛ ብዙሃን አዘጋጅ ያያሰው ሽመልስ ነው። ከ11 ቀናት በፊት ግንቦት 18፤ 2014 ከመኖሪያ ቤቱ በፖሊስ የተያዘው ያየሰው፤ ፍርድ ቤት ሲቀርብ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። 

ጋዜጠኛ ያየሰው በፖሊስ በተያዘ ማግስት በተገኘበት የችሎት ውሎ፤ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ለፖሊስ 10 የምርመራ ቀናትን ፈቅዶ ነበር። ዛሬ ሰኞ ግንቦት 29 በነበረው የችሎት ውሎ፤ መርማሪ ፖሊስ አከናውኛቸዋለሁ ካላቸው ተግባራት መካከል፤ ተጠርጣሪው “ሲያስተላልፍ የነበረውን ቪዲዮ አውርደናል” የሚለው ይገኝበታል። 

ፖሊስ በተፈቀዱለት የምርመራ ቀናት፤ ለባንኮች እና ለተለያዩ የመንግስት ተቋማት ደብዳቤ መጻፉንም ለችሎቱ አስታውቋል። ለተጠርጣሪው የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ አካላትን ለመያዝ እና ገንዘቡ ለምን ዓላማ እንደዋለ ለማጣራት 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለትም ችሎቱን ጠይቋል። 

የያየሰው ጉዳይ “መታየት ያለበት በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ነው” ሲሉ የተከራከሩት የጋዜጠኛው ጠበቃው አቶ ታደለ ገብረመድህን፤ “እስሩ የዘፈቀደ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። በችሎት ፊት ለመናገር እድል ያገኘው ጋዜጠኛ ያየሰው በበኩሉ፤ ለፖሊስ ቃል በሚሰጥበት ወቅት “ከሁለት ዓመት በፊት መንግስትን ሆድ የሚያስብስ ነገር ተናግረሃል” መባሉን ገልጿል።

“በ2013 መንግስት ‘ሞቷል’ ያለውን ግለሰብ፤ በ2014 በስልክ አናግረሃል ተብያለሁ” በማለትም በምርመራ ወቅት ያጋጠመውን ለችሎቱ አስረድቷል። ከዚህም በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በአዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ ታስሮ በነበረበት ወቅት ይቀርቡለት የነበሩት ጥያቄዎች እንደሚቀርቡለትም ተናግሯል። ጋዜጠኛ ያየሰው፤ ባለፈው ዓመት መጨረሻ አካባቢ ከሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር በአፋር ክልል በአዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ በሚገኝ የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ ለ49 ቀናት ከታሰረ በኋላ በዋስትና ከእስር መውጣቱ ይታወሳል።

በጋዜጠኛ ያየሰው እና በጠበቃው በኩል ለቀረቡት መከራከሪያዎች መርማሪ ፖሊስ በሰጠው ምላሽ “እየመረመርን ያለነው ሚዲያ አይደለም። እየመረመርን ያለነው የተደራጀ ወንጀል ነው። የሀገር ጉዳይ ነው” ሲል ለችሎቱ ገልጿል። የተጠርጣሪ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ ጠበቆቻቸውን እና የመርማሪ ፖሊስ ክርክር ያደመጠው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤  የምርመራ መዝገቡን መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለነገ ጠዋት ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት የዛሬውን የችሎት ውሎ አጠናቅቋል። በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ አምስቱም ተጠርጣሪዎች በአካል ተገኝተው የችሎት ሂደቱን ተከታትለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)