በሃሚድ አወል
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ ሰለሞን ሹምዬ እና መዓዛ መሐመድ እያንዳንዳቸው የ10 ሺህ ብር ዋስትና በማስያዝ ከእስር እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጠ። ፍርድ ቤቱ፤ ፖሊስ በጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ እና በመስከረም አበራ ላይ እያካሄድኩት ነው ላለው ምርመራም ተጨማሪ ስድስት ቀናት ፈቅዷል።
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 30፤ 2014 ትዕዛዙን ያስተላለፈው፤ በተለያየ መዝገብ የቀረበለትን የፖሊስ የምርመራ ሂደት ከመረመረ በኋላ ነው። የዋስትና መብቱ በመጀመሪያ የተሰጠው ለ“ፍትሕ” መጽሄት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ ነው።
ችሎቱ ተመስገን በ10 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈታ የወሰነው በሁለት ምክንያቶች ነው። የመጀመሪያው ምክንያት ለፖሊስ በተሰጠው የምርምራ ጊዜ “በቂ ስራ ተሰርቷል ማለት ስለማይቻል” መሆኑን ችሎቱ አስታውቋል። ሁለተኛው ምክንያት ጋዜጠኛ ተመስገን የተጠረጠረበት “በመገናኛ ብዙሃን ሁከት እና ብጥብጥ የማነሳሳት ወንጀል” ባለፈው ዓመት በጸደቀው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ የሚታይ መሆኑ ነው።
በችሎቱ የተጠቀሰው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ “በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል፤ በወንጀል ስነ ስርዓት ሕግ ድንጋጌዎች መሰረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዐቃቤ ህግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ አለበት” ሲል ይደነግጋል። ጋዜጠኛ ተመስገን በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለበት ግንቦት 18 ጀምሮ ለ12 ቀናት በእስር ቆይቷል።
በዛሬው የችሎት ውሎ ከተመስገን በመቀጠል ጉዳዩ የታየለት ጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬ ነው። ከ18 ቀናት በፊት በፖሊስ የተያዘው ሰለሞን ሹምዬ እንደ ተመስገን ደሳለኝ ሁሉ የተጠረጠረው ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል ነው።
“ገበያኑ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነው ሰለሞን በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ዛሬን ጨምሮ ለአራት ጊዜ ያህል ፍርድ ቤት ቀርቧል። የሰለሞንን የጊዜ ቀጠሮ ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም በነበሩት ችሎቶች ለፖሊስ የዘጠኝ እና ሰባት ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቅዶ ነበር።
የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ በዛሬ ውሎው ለፖሊስ “ሌላ ተጨማሪ ጊዜ መፍቀድ አስፈላጊ ሆኖ አለማግኘቱን” ገልጿል። በዚህም መሰረት ሰለሞን በራሱ አንደበት እና በጠበቃው በኩል ያቀረበውን የዋስትና ጥያቄ ተቀብሎ፤ 10 ሺህ ብር በማስያዝ ከእስር እንዲለቀቅ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
“ሮሃ ሚዲያ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት መዓዛ መሐመድም በተመሳሳይ በዛሬው ችሎት በአስር ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንድትለቀቅ በፍርድ ቤት ተወስኖላታል። መዓዛ ከጓደኛዋ መኖሪያ ቤት በፖሊስ የተያዘችው ከአስር ቀናት በፊት ግንቦት 20፤ 2014 ነበር።
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለመዓዛ መሐመድ፣ ለሰለሞን ሹምዬ እና ተመስገን ደሳለኝ ዋስትና ቢፈቅድም፤ በሌሎች ሁለት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ላይ ግን ተጨማሪ ምርመራ ለማከናወን በፖሊስ የቀረበውን ጥያቄ ተቀብሏል። በትላንትናው ዕለት በነበረው ችሎት፤ ፖሊስ በመስከረም አበራ እና ያየሰው ሽመልስ ላይ እያካሄደው ላለው ምርመራ ተጨማሪ 14 ቀናት መጠየቁ ይታወሳል።
የሁለቱን የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የምርመራ መዝገብ መመልከቱን የገለጸው ችሎቱ፤ “ፖሊስ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ስራዎችን መስራቱን ያሳያል” ብሏል። “አልፎ አልፎ” የሚቀሩ ስራዎች መኖራቸውን የጠቆመው ችሎቱ፤ ፖሊስ ቀሪ ስራዎቹን አጠናቆ እንዲያቀርብ ስድስት ተጨማሪ የምርመራ ቀናትን ፈቅዷል።
“ኢትዮ ንቃት” የተሰኘ የዮቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነችው መስከረም አበራ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለችው ከ17 ቀናት በፊት ግንቦት 13፤ 2014 ነበር። በመስከረም ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሲፈቀድ ይህ ለሁለተኛ ጊዜው ነው። ከሁለት ሳምንት በፊት ግንቦት 16 በዋለው ችሎት፤ በተጠርጣሪዋ ላይ እየተካሄደ ያለው ምርመራ “ጅምር ስለሆነ እና ብዙ የሚሰሩ ስራዎች” የሚቀሩ መሆናቸውን በመጥቀስ ፍርድ ቤቱ 13 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቅዶ ነበር።
በተመሳሳይ በጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ ላይም ለፖሊስ የምርመራ ጊዜ ሲፈቀድ የዛሬው ሁለተኛ ጊዜ ነው። ያየሰው ከአስር ቀናት በፊት ግንቦት 19፤ 2014 ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ለፖሊስ 10 የምርመራ ቀናት ተፈቅዶለት ነበር።
የ“ኢትዮ ፎረም” የዩቲዩብ መገናኛ ብዙሃን አዘጋጅ የነበረው ያየሰው ለእስር ሲዳረግ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜው ነው። ያየሰው ለመጨረሻ ጊዜ የታሰረው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ነበር። ጋዜጠኛው ከሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር በአፋር ክልል በአዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ በሚገኝ የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ ለ49 ቀናት ከታሰረ በኋላ በዋስትና ከእስር መውጣቱ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)