መንግስት ከ2015 በጀት 69 በመቶውን ለዕዳ ክፍያ፣ ለመከላከያ፣ ለዕለት ዕርዳታ እና ለማዳበሪያ ድጎማ መደበ

⚫ 231 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት እንደሚያጋጥም ተገምቷል

የፌደራል መንግስት ለ2015 ከመደበው በጀት ውስጥ 69 በመቶው፤ ለዕዳ ክፍያ፣ ለመከላከያ፣ ለዕለት ዕርዳታ እና ለማዳበሪያ ድጎማ የተያዘ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ አስታወቁ። መንግስት ለእነዚህ ጉዳዮች የመደበው በጀት “ከፍተኛ ጭማሪ” በማሳየቱ ምክንያትም፤ ለመንገድ፣ ለትምህርት፣ ለውሃና ኢነርጂ፣ ለጤና፣ ለከተማ ልማት እና ለግብርና ዘርፎች የተመደበው ገንዘብ ቅናሽ አሳይቷል ብለዋል። 

የገንዘብ ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት የ2015 በጀት መግለጫን ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 30፤ 2014 ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ነው። በበጀት መግለጫው መሰረት የፌደራል መንግስት ለ2015 ከበጀተው 786.6 ቢሊዮን ብር ውስጥ፤ 239 ቢሊዮን ብር ያህሉ የተመደበው ለዕዳ ክፍያ፣ ለመከላከያ፣ ለዕለት ዕርዳታ እና ለማዳበሪያ ድጎማ ነው።

እንደ አቶ አህመድ ገለጻ፤ ለዕዳ ክፍያ እና ለመከላከያ ብቻ የተመደበው የወጪ በጀት፤ ከአጠቃላይ የፌደራል መንግስት መደበኛና ካፒታል ወጪ 37.3 በመቶ ያህል ድርሻን ይዟል። የገንዘብ ሚኒስትሩ የ2015 የመንግስት ወጪ “በዕዳ ክፍያ፣ በሰብዓዊ እርዳታ፣ በመልሶ ግንባታና የአገር ደህንነትን የማስጠበቅ አቅም በማጠናከር ላይ” ትኩረት ያደረገ እንደሆነ አብራርተዋል።  

ዛሬ ለተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የቀጣዩ ዓመት በጀት፤ 231.4 ቢሊዮን ብር የተጣራ የበጀት ጉድለት እንደሚያጋጥመው ተገምቷል። የኢትዮጵያ መንግስት የበጀት ጉድለቱን በዋነኛነት ለመሸፈን ያቀደው ከሀገር ውስጥ ከሚወሰድ ብድር ነው።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ለፓርላማ አባላት እንደተናገሩት፤ “የበጀት ጉድለቱ ቀደም ካሉት ዓመታት ከነበረው መጠን አንጻር “በመጠኑ ከፍ ያለ” ነው። የፌደራል መንግስት የበጀት ጉድለቱን ይድፍንለት ዘንድ ከሀገር ውስጥ ምንጮች በብድር ለማግኘት ያቀደው የገንዘብ መጠን 224.5 ቢሊዮን ብር መሆኑ ለፓርላማ በቀረበው የበጀት መግለጫ ላይ ሰፍሯል። 

“ይህም በዋናነት ሀገራችን ካለችበት አንጻር አንገብጋቢ የወጪ ፍላጎቶች መሸፈን የግድ ስለሚል የቀረበ ነው” ሲሉ ሚኒስትሩ ብድሩ ያስፈለገበትን ምክንያት ገልጸዋል። “ሆንም ግን የዋጋ ንረቱ ለማርገብ፤ ብድሩ በተቻለ መጠን በመንግስት ግምጃ ቤት ሽያጭ እንዲወሰድ እና ሌሎች ጠንካራ እርምጃዎችን  ተግባራዊ በማድረግ በዋጋ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል” ሲሉ አቶ አህመድ ተናግረዋል። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)