በኢትዮጵያ ያሉ ተፈላሚ ኃይሎች የሰብዓዊ ዕርዳታ ለተቸገሩ በማድረስ ረገድ ያሳዩትን መሻሻል፤ ግጭቱን በዘላቂነት ወደሚያቆም ውይይት እንዲያሸጋግሩት አሜሪካ ጥሪ አቀረበች። አሜሪካ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አንቶኒ ብሊንከን በኩል ትላንት ማክሰኞ ግንቦት 30 ምሽት ባወጣችው መግለጫ፤ በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ ስራ እንዲጀምሩም ጥሪ አቅርባለች።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በትላንቱ መግለጫቸው፤ ባለፉት ሰባት ቀናት ከ1,100 በላይ ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ትግራይ ክልል መድረሳቸውን አስታውቀዋል። ትግራይ ክልል ከደረሰው ሰብዓዊ እርዳታ ውስጥ በተመጣጠነ ምግብ እጦት የተጎዱ ሰዎችን ለመከም የሚያስፈልጉ ግብዓቶች፣ የህክምና አቅርቦቶች እና ሌሎች አስፈላጊ እርዳታዎች እንደሚገኙበት በመግለጫው ሰፍሯል።
አንቶኒ ብሊንከን በዚሁ መግለጫቸው በአፋር፣ አማራ እና በትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ በመደበኛነት ለማድረስ የታየውን መሻሻል አድንቀዋል። እርዳታው እንዲደርስ በማመቻቸት የኢትዮጵያ መንግስት፣ የአፋር እና የትግራይ ከልሎች ባለስልጣናትን “በተለይ” አመስግነዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት የታየው መሻሻል በሰሜን ኢትዮጵያ ብርቱ ሰብዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀወስ ያስከተለውን ግጭት በዘላቂነት ማቆም ወደሚያስችል ውይይት እንዲሸጋገር ጥሪ አቅርበዋል። “ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ደህንነትን እና ብልጽግናን የሚያረጋግጥ ሁሉን አካታች የፖለቲካ ሂደት እንደግፋለን” ሲሉም ብሊንከን የሀገራቸውን አቋም አስታውቀዋል። በሁሉም ወገኖች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች አጥፊዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ አገራቸው እንደምትሻም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አንስተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)