በአማራ እና አፋር በጦርነት ወቅት የተፈጸሙ ወንጀሎች የመረመረው የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ሪፖርቱን ይፋ ሊያደርግ ነው

በሃሚድ አወል

በሰሜኑ ጦርነት በአማራ እና አፋር ክልሎች የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚመረምረው የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል፤ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የምርመራ ሪፖርቱን ይፋ እንደሚያደርግ አስታወቀ። ግብረ ኃይሉ በምርመራው በሁለቱ ክልሎች ብቻ በሺህዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን መገደላቸውን አረጋግጧል ተብሏል።   

የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ያቋቋመውን ጽህፈት ቤት በኃላፊነት የሚመሩት ዶ/ር ታደሰ ካሳ ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 1፤ 2014 ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የምርመራ ሪፖርቱን ይፋ ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩን ተናግረዋል። የምርመራ ሪፖርቱ “በቁጥርም፤ በአካባቢም ዝርዝር መረጃዎችን” ይዞ እንደሚወጣም ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።  

ለሪፖርቱ ግብዓት የሆኑ “አስፈላጊ” መረጃዎች የተሰበሰቡት፤ የሚኒስትሮች ግብረ ኃይሉ ከሶስት ወራት ገደማ በፊት ባሰማራቸው የምርመራ ቡድኖች ነው። በአማራ እና አፋር ክልል በሚገኙ ዘጠኝ አካባቢዎች የተሰማሩት ቡድኖች 158 አባላት ያሏቸው ናቸው።  

ከዘጠኙ አካባቢዎች ስምንቱ በአማራ ክልል የሚገኙ ሲሆን አንዱ አካባቢ ደግሞ የሰሜኑ ጦርነት ሌላኛው ሰለባ በሆነው የአፋር ክልል ያለ ነው። የሰሜን ሸዋ፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ፣ የዋግ ህምራ ዞን፣ ኮምቦልቻ ከተማ እና አከባቢው፣ ደሴ ከተማ እና አካባቢው፣ ወልዲያ ከተማ እና አካባቢው፣ ላሊበላ ከተማ እና አካባቢው እንዲሁም ጃማ እና ወረኢሉ እያንዳንዳቸው የምርመራ ቡድን የተሰማራባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ናቸው።

ግብረ ኃይሉ ባሰማራቸው የምርመራ ቡድኖች አማካኝነት ሲያሰባስባቸው የቆያቸውን መረጃዎች የመተንተን ሂደት፤ በቀረው የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የሚከናወን መሆኑን ዶ/ር ታደሰ አስረድተዋል። ትንተናውን ተከትሎም ግብረ ኃይሉ “የትኛው ማስረጃ የትኛውን ወንጀል ነው የሚደግፈው እና የሚያስረዳው” የሚለውን እንደሚወስን የጽህፈት ቤት ኃላፊው ገልጸዋል። በምርመራው ሂደት “ወንጀል ፈጽመዋል” ተብለው የተለዩ ግለሰቦች ላይ ክስ ለመመስረት ቅድመ ዝግጅቶች ማካሄድ ሌላው ተጨማሪ ስራ እንደሆነም አክለዋል።

እስካሁን በተደረገው የምርመራ ሂደት በሺህዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን መገደላቸው መረጋገጡን የገለጹት ዶ/ር ታደሰ፤ በሁሉም ላይ የተፈጸመው “ከዳኝነት ውጭ የሆነ ግድያ” “አሰቃቂ” እንደነበር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። በዚሁ በጦርነት ወቅት “ከሺህ ከፍ የሚሉ ሰዎች” የጾታዊ ጥቃት ሰለባ መሆናቸውንም የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ጽህፈት ቤት ኃላፊው አመልክተዋል።

ዶ/ር ታደሰ “በታሪካችን አይተነው የማናውቀው አይነት pattern ያየንበት” ሲሉ የገለጹት ጾታዊ ጥቃት በዋናነት የተፈጸመው “በህወሓት በኩል” መሆኑንም አመልክተዋል። “ላለፉት አራት እና አምስት ወራት ለረዥም ጊዜ ሲሰራ የቆየው በዋናነት በህወሓት በኩል የተፈጸሙ ወንጀሎች ላይ ትኩረት ያደረገ የምርመራ ስራ ነው” ሲሉም የጽህፈት ቤት ኃላፊው የምርመራ ሂደቱን አስረድተዋል።  

ግብረ ኃይሉ በትግራይ ክልል የተፈጸሙ ወንጀሎችን በተመለከተ ምርመራ ለማድረግ እቅድ ይኖረው እንደሆነ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር ታደሰ፤ የምርመራ ቡድን ለማሰማራት በመጀመሪያ የቡድኑን አባላት ደህንነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል። “አሁን በትግራይ ያለው ሁኔታ ያንን ይፈቅዳል ብሎ ማሰብ ያስቸግራል። ሰላም ነው ብሎ ቢታሰብ እንኳን የፖለቲካ ሂደቱ ያንን አይፈቅድም” ያሉት የጽህፈት ቤት ኃላፊው፤ “ግብረ ኃይሉ ከሚሰራው የቴክኒክ ስራ በፊት፤ ግዴታ የፖለቲካ ሂደቱ መቅደም አለበት” ሲሉ ከምርመራ በፊት በመጀመሪያ መከናወን የሚገባው ጉዳይ መኖሩን አመልክተዋል። 

ዶ/ር ታደሰ “ነባራዊ ሁኔታው ሲፈቅድ” የሚኒስትሮች ግብረ ኃይሉ የምርመራ ቡድን ወደ ትግራይ እንደሚያሰማራም ጠቁመዋል። በግብረ ኃይሉ ስር ከተቋቋሙት አራት ኮሚቴዎች አንዱ የሆነው የወንጀል ምርመራ እና ማስቀጣት ኮሚቴ፤ የትግራይ ክልልን የምርመራ ስራ የሚያከናውን አንድ ቡድን “በተጠንቀቅ” አዘጋጅቶ እየተጠባበቀ እንደሚገኝም ገልጸዋል። 

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወቅት በአማራ እና አፋር ክልል የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚያጣራው የሚኒስትሮች የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አማካኝነት የተቋቋመው ከሰባት ወራት በፊት ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግብረ ኃይሉ እንዲቋቋም ያደረጉት፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጽህፈት ቤት ጋር በጥምር ያደረጉትን የምርመራ ውጤት ይፋ ካደረጉ በኋላ ነው። 

ሁለቱ የሰብዓዊ መብት ተቋማት በጥምር የምርመራ ሪፖርታቸው፤ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተሳተፉ ሁሉም አካላት የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን አስታውቀው ነበር። በግጭቱ ተሳታፊዎች በተለያየ መጠን ተፈጽመዋል ከተባሉት ጥሰቶች ውስጥ “የጦር ወንጀሎች” እና “በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች” ይገኙበታል። ሁለቱ ተቋማት ተፈጽመዋል ላሏቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፤ የፌደራሉ መንግስት “ገለልተኛ፣ ፈጣን እና ውጤታማ” ምርመራ እንዲያከናውን ምክረ ሃሳብ አቅርበው እንደነበርም ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)