ለኢዜማ አመራርነት የሚወዳደሩ ዕጩዎች ከዛሬ ጀምሮ የምረጡኝ ቅስቀሳ ሊያደርጉ ነው

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) በተያዘው ሰኔ ወር በሚያካሄደው መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ለፓርቲው አመራርነት የሚወዳደሩ ዕጩዎችን አስተዋወቀ። ፓርቲው ያስተዋወቀው ለኢዜማ መሪነት፣ ሊቀመንበርነት፣ ጸሐፊነት እንዲሁም ለፋይናንስ ኃላፊነት የሚወዳደሩ ዕጩዎችን ነው።

ዕጩዎቹ ከዛሬ ረቡዕ ሰኔ 1፤ 2014 ጀምሮ እስከ ሰኔ 24 ድረስ በኢዜማ የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች “የምረጡኝ ቅስቀሳ” እንደሚያደርጉ የፓርቲው አስመራጭ ኮሚቴው አስታውቋል። ለምርጫ የቀረቡት ግለሰቦች ዛሬ ከሰዓት በኋላ በአዲስ አበባ ስቴዲየም አካባቢ በሚገኘው የኢዜማ ዋና ጽህፈት ቤት በአካል ተገኝተው የምርጡኝ ቅስቀሳ የሚያደርጉበትን የሰዓት ድልድል ዕጣ አውጥተዋል።

ለኢዜማ መሪነት ለመወዳደር ሶስት ግለሰቦች በዕጩነት ቀርበዋል። ከሶስቱ ዕጩዎች ሁለቱ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ሲሆኑ አንደኛው ዕጩ ደግሞ በአባልነት ደረጃ የሚገኙ ናቸው። ለመሪነት የሚወዳደሩት ሁለቱ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ዕጩዎች ኢዜማን ከምስረታው ጀምሮ በመሪነት እየመሩ የሚገኙት ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ እና ምክትላቸው አቶ አንዷለም አራጌ ናቸው።

ሶስተኛው ዕጩ አቶ ጸጋው ታደለ ለመሪነት ለመወዳደር ከአዲስ አበባ ውጭ የቀረቡ ብቸኛው ግለሰብ ናቸው። የ32 ዓመቱ አቶ ጸጋው በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ያቤሎ ከተማ በሚገኝ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ናቸው። አቶ ጸጋው ለመሪነት በሚደረገው ውድድር ከክልል በመቅረብ ብቻ ሳይሆን ያለምክትልም በመቅረብ ብቸኛው ናቸው።

የእኚህ ምክትል ሆነው በዕጩነት ቀርበው የነበሩት አቶ አየለ ዳመነ “የፓርቲውን የውስጥ መስፈርት ባለማሟላታቸው” ከውድድር ውጭ መሆናቸውን አቶ ጸጋው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ለመሪነት የሚወዳደሩት ቀሪ ሁለቱ ዕጩዎች ምክትል መሪዎች ያሏቸው ሲሆን፤ አቶ ዮሃንስ መኮንን የፕ/ር ብርሃኑ፤ አቶ ሀብታሙ ኪታባ ደግሞ የአቶ አንዷለም ምክትል ሆነው ቀርበዋል።

የኢዜማ ሊቀመንበር ለመሆን አምስት ዕጩዎች ለውድድር መቅረባቸው ይፋ ተደርጓል። ከዕጩዎቹ መካከል የአሁኑ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ እና ምክትላቸው ዶ/ር ጫኔ ከበደ ይገኙበታል። አነስተኛ የዕጩ ቁጥር የቀረበበት የፓርቲው ጸሐፊነት ቦታ ሲሆን አሁን በኢዜማ ፀሐፊነት የሚያገለግሉት አቶ አበበ አካሉ እና አቶ መሐመድ ይመር ለቦታው ይወዳደራሉ። በአጠቃላይ ለፓርቲው ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ምርጫ ለውድድር ከቀረቡ 23 ዕጩዎች መካከል ሴቶቹ ሁለት ብቻ ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)