ዓለም አቀፉ የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጽ ፌስቡክ፤ በኢትዮጵያ ሶስት ብሔሮች ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ ንግግሮች ያዘሉ ማስታወቂያዎች ይለይ እንደሁ የተሰጠውን ፈተና ወደቀ። ግዙፉን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ የሙከራ ማስታወቂያዎችን በመጠቀም የፈተኑት “ግሎባል ዊትነስ” እና “ፎክስ ግሎቭ” የተባሉ ሁለት ተቋማት ከቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር ዳግም አፈወርቅ ጋር በመተባበር ነው።
የሁለቱ ተቋማት እና የመምህሩን የጋራ የምርመራ ውጤት ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 2፤ 2014 ይፋ ያደረገው ተቀማጭነቱ በለንደን የሆነው “ግሎባል ዊትነስ” የተሰኘው ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው። ምርመራው የተከናወነው፤ የፌስቡክ የጥላቻ ንግግር መለያ ምን ያህል ጥሩ እንደሆነ ለመፈተን እና የኩባንያው የደህንነት መቆጣጠሪያ ስልቶች ሁከት የሚያባብሱ ማስታወቂያዎችን መከላከል ይችል እንደሁ ለመፈተሽ እንደሆነ ድርጅቱ አስታውቋል።
በአማርኛ ቋንቋ በፌስቡክ የተጻፉ 12 የከፉ የጥላቻ ንግግሮችን የለዩት ምርመራ አድራጊዎቹ፤ እነዚሁኑ ይዘቶች ለኩባንያው እንደ ማስታወቂያ በማቅረብ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴው ለመለጠፍ ይፈቅድላቸው እንደሁ ሙከራ አድርገዋል። በምሳሌነት የተለዩት ሁሉም የጥላቻ ንግግሮች ከዚህ ቀደም የፌስቡክን የአጠቃቀም መመሪያዎች ጥሰው በመገኘታቸው “ሪፖርት ተደርገው አብዛኞቹ የተወገዱ መሆናቸውን” “ግሎባል ዊትነስ” ገልጿል።
የኩባንያውን የቁጥጥር አቅም ለመፈተሽ በምሳሌነት የተመረጡት የጥላቻ ንግግሮች የተካተቱባቸው ማስታወቂያዎች፤ የአማራ፣ የትግራይ እና የኦሮሞ ብሔሮች ላይ እኩል ያነጣጠሩ ናቸው። በማስታወቂያዎቹ አረፍተ ነገሮች መካከል “ሰዎች እንዲገደሉ፣ እንዲራቡ ወይም ከአንድ አካባቢ እንዲጠፉ በቀጥታ ጥሪ የሚያደርጉ፤ ሰዎችን ከእንስሳት ጋር የሚያነጻጽሩ እና ሰብዓዊነት የጎደላቸው” ገለጻዎች እንዳሉበት በ“ግሎባል ዊትነስ” መግለጫ ተጠቅሷል።
አብዛኞቹ የማስታወቂያዎቹ ይዘቶች የዘር ማጥፋት እንዲፈጸም ጥሪ የሚያቀርቡ መሆናቸውን የገለጸው ድርጅቱ፤ ከእነርሱ ውስጥ አንዳቸውም ለመተርጎም ውስብስብ እንዳልነበሩም ድርጅቱ ጠቁሟል። “የትኞቹንም ማስታወቂያዎች አላተምናቸውም። የሚታተሙበትን ቀን ወደ ፊት እንዲሆን በማድረግ፤ ፌስቡክ ማስታወቂያዎቹን መቀበል እና አለመቀበሉን ካሳወቀን በኋላ አጥፍተናቸዋል” ሲል “ግሎባል ዊትነስ” የጥላቻ ንግግሮቹ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴው ለህዝብ ይፋ አለመደረጋቸውን አረጋግጧል።
በምርመራው መሰረት ፌስቡክ የቀረበሉትን አስራ ሁለቱንም የጥላቻ ንግግሮች፤ በማስታወቂያ መልክ በገጹ እንዲቀርቡ ፈቃድ ሰጥቷል። ሁሉም ማስታወቂያዎች ፌስቡክ በአጠቃቀም መመሪያው (community standards) የጥላቻ ንግግር ብሎ ከሚበይናቸው ውስጥ የሚካተቱ ናቸው። በሙከራ ደረጃ ፌስቡክ የተፈተነባቸው ማስታወቂያዎች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴው ላይ ለዕይታ ቢበቁ ኖሮ፤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ከ57 አመታት በፊት የጸደቀውን ስምምነት የሚጥሱ ነበሩ። ስምምነቱ ማናቸውም አይነት የዘር መድሎዎ ለማስወገድ የጸደቀ ነው።
በድርጅቶቹ ምርመራ የተገኘው ውጤት በስተመጨረሻ የቀረበለት ፌስ ቡክ፤ ማስታወቂያዎቹ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴው እንዲታተሙ መፈቀድ እንዳልነበረበት ማመኑን “ግሎባል ዊትነስ” በመግለጫው ጠቅሷል። ፌስቡክ ለኢትዮጵያ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች የደህንነት ቁጥጥሩን ለማጥበቅ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን መግለጹንም ምርመራውን ካከናወኑት ድርጅቶች አንዱ የሆነው “ግሎባል ዊትነስ” አመልክቷል።
ፌስቡክ ከሶስት ዓመታት ገደማ በፊት ኢትዮጵያን ከፍተኛ የግጭት እና የሁከት ስጋት ካለባቸው አገራት ጎራ እንደመደበ በጥቅምት 2013 አስታውቆ ነበር። ከኢትዮጵያ ህዝብ 10 በመቶ ብቻ የፌስቡክ ተጠቃሚ እንደሆነ የገለጸው ዓለም አቀፉ ኩባንያ፤ በአገሪቱ በሚነገሩ ቋንቋዎች ብዛት “ከፖሊሲዎቹ የሚጣረሱ ይዘቶችን ለማስወገድ፣ የሰዎችን ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ለማስከበር እና ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ” ያስቀመጣቸውን የትኩረት አቅጣጫዎች ተግባራዊ ለማድረግ መቸገሩን በወቅቱ መግለጹ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)