ለተመስገን ደሳለኝ፣ ሰለሞን ሹምዬ እና መዓዛ መሐመድ የተፈቀደው የ10 ሺህ ብር ዋስትና ተሻረ

በሃሚድ አወል

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ ሰለሞን ሹምዬ እና መዓዛ መሐመድ በስር ፍርድ ቤት የተፈቀደላቸውን የ10 ሺህ ብር ዋስትና ሻረ። ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን የሻረው፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በዋስትና ትዕዛዙ ላይ ይግባኝ ካቀረበ በኋላ ነው። 

የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 2፤ 2014 ከሰዓት በጽህፈት ቤት በኩል በሰጠው ትዕዛዝ ለመርማሪ ፖሊስ የ8 ቀናት የምርመራ ጊዜን ፈቅዷል። “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት” ወንጀል የተጠረጠሩት የሶስቱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጉዳይ ለዛሬ ረፋድ ተቀጥሮ የነበረው፤ በመርማሪ ፖሊስ የቀረበውን ይግባኝ መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ነበር። 

ሶስቱም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች  ከጠበቃቸው አቶ ሔኖክ አክሊሉ ጋር በፍርድ ቤት በአካል ቢገኙም፤ ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ በስራ መደራረብ ምክንያት ምርመራውን አለመጠናቀቁን አስታውቋል። የችሎቱ ዳኛ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማስረጃ ናቸው ያላቸውን ሰነዶችን፣ ሲዲ እና “ፍላሽ” በሶስቱም ተጠርጣሪዎች መዝገብ ማያያዙን ገልጸው፤ እነዚህን መመርመር በማስፈለጉ ትዕዛዝ መስጠቱን ለከሰዓት ማዛወራቸውን ገልጸዋል። 

መርማሪ ፖሊስ በተመስገን ደሳለኝ እና ሰለሞን ሹምዬ መዝገቦች ማስረጃዎቹን ያያያዘው በሲዲ ሲሆን በመዓዛ መሐመድ ላይ ደግሞ በ“ፍላሽ” ነው። በመርማሪ ፖሊስ አማካኝነት ለፍርድ ቤቱ የቀረቡት የእነዚህ ማስረጃዎች ምንነት ግን በችሎቱም ሆነ በፖሊስ አልተገለጸም። 

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በትላንትናው ዕለት በነበረ የችሎት ውሎ፤ ለሶስቱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በስር ፍርድ ቤት በተፈቀደው ይግባኝ ውድቅ እንዲደረግ እና 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ነበር። የኮሚሽኑ መርማሪ ፖሊሶች ተመስገንም ሆነ ሌሎቹ ሁለት ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበት ወንጀል “ውስብስብ፣ በሀገር ላይ እና በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለ ነው” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ባስገቡት ማመልከቻ ጠቅሰዋል።

መርማሪዎቹ በትላንትናው ችሎት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የተጠረጠረበት “ሁከት እና ብጥብጥ ማነሳሳት” ወንጀል ወደ “ሽብር ወንጀል” ሊቀየር እንደሚችልም ጥቆማ ሰጥተዋል። መርማሪዎቹ ይህን ያሉት ተመስገን የተጠረጠረበት ወንጀል ውስብስብ መሆኑን ለፍርድ ቤት ባስረዱበት ወቅት ነው።

ከዚህ አንጻር ምርመራው “ሰፊ ጊዜ የሚጠይቅ” በመሆኑ እና ምርመራውን በስፋት እስኪያጣሩ ድረስ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸው የስር ፍርድ ቤት መጠየቃቸውን መርማሪ ፖሊሶቹ አስታውሰዋል። ሆኖም የስር ፍርድ ቤቱ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ግንቦት 30፤ 2014 በዋለው ችሎት ለእያንዳንዳቸው ተጠርጣሪዎች የ10 ሺህ ብር ዋስትና መፍቀዱን እንደሚቃወሙ መርማሪዎቹ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ገልጸዋል። 

ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ውድቅ አድርጎ ሶስቱን የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ ትዕዛዙን ያስተላለፈው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው። መርማሪዎቹ ይህንን የተጨማሪ የምርመራ ቀናት ጥያቄ በድጋሚ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት አቅርበዋል። 

በትላንትናው የችሎት ውሎ የፖሊስን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጥያቄ አጥብቀው የተቃወሙት የተጠርጣሪ ጠበቆች፤ ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ የስር ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን የዋስትና ትዕዛዝ እንዲያጸና ጥያቄ አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱ የፖሊስን ይግባኝ እና የጠበቆችን ምላሽ መርምሮ ዛሬ ሐሙስ ከሰዓት በሰጠው ትዕዛዝም፤ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ሽሯል። 

ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ የፖሊስን የተጨማሪ የምርመራ ቀናት ጥያቄ ተቀብሏል። ሆኖም ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀናት በመቀነስ፤ ስምንት ቀናት ብቻ ፈቅዷል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፖሊስን የምርመራ ውጤት ለማድመጥ ለሰኔ 10፤ 2014 ቀጠሮ በመስጠት የዛሬውን የችሎት ውሎ አጠናቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)