በሃሚድ አወል
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በእስር ላይ የሚገኘው የጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ጉዳይ መታየት ያለበት “በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ነው” በሚል በተጠርጣሪው ጠበቃ ለቀረበለት አቤቱታ የፖሊስን ምላሽ ለመቀበል ለመጪው ረቡዕ ሰኔ 8፤ 2014 ቀጠሮ ሰጠ። ፍርድ ቤቱ ቀጠሮውን የሰጠው፤ በትላንትናው ዕለት በመርማሪ ፖሊስ በተጠየቀው ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናት ጉዳይ ላይ ትዕዛዝ ሳይሰጥ ነው።
አራት ኪሎ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ግንቦት 19፤ 2014 በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ጋዜጠኛ በቃሉ፤ በፍርድ ቤት የተፈቀደበትን 12 ቀናት የምርመራ ጊዜ ያጠናቀቀው ትላንት ሐሙስ ነበር። የጋዜጠኛውን ጉዳይ የሚመለከተው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ ፖሊስ በተፈቀዱለት የምርመራ ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት ለማድመጥ ለትላንት ሰኔ 2 ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።
መርማሪ ፖሊስ በትላንትናው ዕለት በጹሁፍ ለችሎቱ ባስገባው ደብዳቤ፤ “ወንጀሉ ውስብስብ በሀገር ላይ እና በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለ” እና “ሰፊ ጊዜ የሚጠይቅ መሆኑን” በመጥቀስ ፍርድ ቤቱ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቅድለት ጠይቋል። ፖሊስ ተጨማሪ ጊዜውን ከጠየቀባቸው ምክንያቶች አንዱ ተጠርጣሪውን በተለያዩ መንገዶች በገንዘብ እየረዱ ያሉ ግለሰቦችን በመለየት በቁጥጥር ስር ለማዋል መሆኑን አስታውቋል።
ፍርድ ቤቱ በፈቀደለት የምርመራ ቀናት ከተጠርጣሪው እጅ የተያዙ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ለምርመራ ቢልክም ውጤቱን እስካሁን አለማግኘቱን ለፍርድ ቤት የገለጸው ፖሊስ፤ “ውጤቱ ተሰርቶ እስኪመጣ” ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠውም ጠይቋል። ፖሊስ ከዚህ በተጨማሪም፤ ለመንግስት እና ለግል ባንኮች ለላካቸው ደብዳቤዎች ምላሽ ለመጠባበቅ እና “ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች” ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ማስረጃዎች ለማሰባሰብ ተጨማሪ ቀናት እንደሚያስፈልጉት ለችሎቱ አስረድቷል።
የጋዜጠኛ በቃሉ ጠበቃ አቶ ታደለ ገብረ መድህን በበኩላቸው “ጉዳዩ በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ” መታየት እንዳለበት ጠቅሰው፤ “ችሎቱም ጉዳዩን አይቶ የጊዜ ቀጠሮ የመስጠት መብት የለውም” ሲሉ በትላንቱ የችሎት ውሎ መከራከሪያ አቅርበው ነበር። የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የጠበቃውን መከራከሪያ ተመልክቶ ትዕዛዝ ለመስጠት ለዛሬ አርብ ሰኔ 3፤ 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፤ ዛሬም በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ሳያስተላለፍ ቀርቷል።
ፍርድ ቤቱ በጽህፈት ቤት በኩል ባካሄደው በዛሬው ችሎት፤ ትዕዛዝ ከማስተላለፉ በፊት የተጠርጣሪው ጠበቃ ባቀረቡት መከራከሪያ ላይ መርማሪ ፖሊስ አስተያየቱን እንዲያቀርብ አምስት ቀናት ሰጥቷል። “አልፋ ቴሌቪዥን” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙሃን መስራች እና ባለቤት የሆነው በቃሉ የዛሬውን የችሎት ውሎ የተከታተለው ያለጠበቃ ነው።
በቃሉ በቁጥጥር ስር የዋለው “ሁከት እና ብጥብጥ” በማነሳሳት ተጠርጥሮ እንደሆነ ፖሊስ ከዚህ ቀደም ለፍርድ ቤት ማስታወቁ አይዘነጋም። “አውሎ ሚዲያ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን ዋና አዘጋጅ የነበረው በቃሉ ከዚህ በፊት ለሁለት ጊዜያት ያህል ለእስር ተዳርጎ ነበር። ጋዜጠኛው “ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት እና የመንግስት ስም በማጥፋት ወንጀል” ተጠርጥሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የታሰረው በጥቅምት 2013 ዓ.ም ነበር።
ባለፈው ዓመት መጨረሻ ገደማ በድጋሚ ለእስር የተዳረገው በቃሉ፤ ከሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር በመሆን ለ49 ቀናት በእስር አሳልፏል። በቃሉን ጨምሮ 13 የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በእስር ላይ የቆዩት በአፋር ክልል አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ በሚገኝ የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ ነበር። የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ የታሰሩት “ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል” በሚል ተጠርጥረው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)