ፋቱዋ ቤንሱዳ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ከሚመረምረው ኮሚሽን ኃላፊነታቸው ለቀቁ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት፤ በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲመረምር ያቋቋመውን ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ኮሚሽን በሊቀመንበር ሲመሩ የነበሩት ፋቱዋ ቤንሱዳ ከኃላፊነታቸው ለቀቁ። በምትካቸው ኬንያዊቷ የህግ ባለሙያ ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ ተሹመዋል።

ጋምቢያዊቷ ፋቱዋ ቤንሱዳ ለምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት በጻፉት እና “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው ደብዳቤ፤ ከዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ኮሚሽን ሊቀ መንበርነታቸውም ሆነ ከአባልነታቸው መልቀቃቸውን አሳውቀዋል። ቤንሱዳ ከኃላፊነታቸው የለቀቁት፤ በብሪታኒያ እና በጋራ ብልጽግና (ኮመን ዌልዝ) አገራት  የጋምቢያ ከፍተኛ ኮሚሽነር ሆነው በሀገራቸው መንግስት በመሾማቸው፤ የጥቅም ግጭትን ለማስወገድ እንደሆነ በደብዳቤያቸው ጠቅሰዋል።

በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም በአቃቤ ህግነት ያገለገሉት ቤንሱዳ ይዘውት የነበረው የባለሙያዎች ኮሚሽን የሊቀመንበርነት ቦታ፤ ኬንያዊቷ ጠበቃ  ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ ተረክበውታል። ኬንያዊቷን ለቦታው የሾሙት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፌዴሪኮ ቪሌጋስ ናቸው።

የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት፤ በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብዓዊ መብት እና ሌሎች ጥሰቶችን ለመመርመር ላቋቋመው ኮሚሽን ሶስት አባላት የሾመው ባለፈው የካቲት 23፤ 2014 ነበር። ከፋቱዋ ቤንሱዳ እና ከካሪ ቤቲ ሙሩንጊ ሌላ የኮሚሽኑ አባል የሆኑት አሜሪካዊው የህግ ባለሙያ ስቴቨን ራትነር ናቸው። 

የተመድ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት መርማሪ ኮሚሽኑ እንዲቋቋም ባለፈው ታህሳስ ወር በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ልዩ ስብሰባ በጠራ ወቅት ከኢትዮጵያ በርቱ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። ታህሳስ 8፤ 2014 በተካሄደው የሰብዓዊ መብት ምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ፤ ከ47 አባል ሀገራት መካከል አስራ አምስቱ ኮሚሽን የሚያቋቋመውን የውሳኔ ሃሳብ መቃወማቸው ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)