በሃሚድ አወል
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀሰው የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ሊቀመንበር አቶ ግራኝ ጉደታ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጋቸውን በካማሺ ዞን የካማሺ ወረዳ ሰላም ግንባታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። የንቅናቄው ሊቀመንበር በቁጥጥር ስር የዋሉት የጉህዴን ታጣቂዎች በካማሺ ዞን “አመጽ ለማነሳሳት ሞክረዋል” በሚል ነው።
የጉህዴን ሊቀመንበር በካማሺ ከተማ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ የተወሰዱት ትላንት አርብ ሰኔ 3፤ 2014 እንደሆነ የካማሺ ወረዳ ሰላም ግንባታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሳቀታ አመንቴ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት “ለእርቅ እየሰራ” ባለበት ወቅት፤ የጉህዴን ታጣቂዎች “አመጽ ለማነሳሳት ሞክረዋል” ሲሉ የሰላም ግንባታ ጽህፈት ቤት ኃላፊው ወንጅለዋል።
የጉህዴን ታጣቂዎች “መንግስት እንደሌለ ቆጥረው በዞን ደረጃ ላይ የበላይነትን ለመውሰድ እየፈለጉ ስለሆነ ለዚህ ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት” ሲሉም የንቅናቄው ሊቀመንበር በቁጥጥር ስር የዋሉበትን ምክንያት ኃላፊው አስረድተዋል። የአቶ ግራኝ ጉደታን መታሰር በጉህዴን ውስጥ ምክትላቸው የሆኑት አቶ ደርጉ ፈረንጅም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።
እንደ አቶ ደርጉ ገለጻ፤ የጉህዴን ሊቀመንበር ለሁለት ሳምንት ገደማ “ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ” በሚል በካማሺ ከተማ በሚገኝ የወጣቶች ማዕከል ጥበቃ እየተደረገላቸው እንዲቆዩ ተደርጎ ነበር። እስክ ትላንት ድረስ ሊቀመንበሩን በስልክ ሲያነጋግሯቸው እንደነበር የጠቆሙት አቶ ደርጉ፤ “ወደ ቤት ሳይመልሱት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱት” ሲሉ የአቶ ግራኝን የእስር ሂደት ገልጸዋል።
“ግልጽ የሆነ ነገር የለም። ዝም ብለው ወስደው [ነው] ያሰሩት። ፖሊሶችም ግልጽ የሆነ ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም” የሚሉት አቶ ደርጉ፤ የጉህዴን ሊቀመንበር በምን ምክንያት እንደታሰሩ የንቅናቄው አመራሮች መረጃ እንደሌላቸው ያስረዳሉ። የአቶ ግራኝን እስር በተመለከተ የክልሉን ኃላፊዎች ለማናገር ጥረት ቢያደርጉም ሊሳካላቸው እንዳልቻለም አክለዋል። ከንቅናቄው ሊቀመንበር በተጨማሪ ሌሎች የጉህዴን አባላት መታሰራቸውን የጠቆሙት አቶ ደርጉ፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እስሮቹን እንዲያጣራ ጠይቀዋል።
የጉህዴን ሊቀመንበርን ጨምሮ ሌሎች የንቅናቄው አመራሮች ለአንድ ዓመት ከስምንት ወር ከታሰሩ በኋላ የተፈቱት ከአራት ወራት በፊት የካቲት አጋማሽ ላይ ነበር። አቶ ግራኝ እና አቶ ደርጉ ከእስር የተፈቱት፤ የጉህዴን ታጣቂዎች ከመንግስት ጋር ዕርቅ ለመፈጸም የአመራሮቹን መፈታት እንደ አንድ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጣቸው ነው።
የአመራሮቹን ከእስር መፈታት ተከትሎ ባለፈው መጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ከጉህዴን ታጣቂዎች ጋር በጉሙዝ ባህል መሰረት በካማሺ ከተማ ዕርቅ መፈጸሙ ይታወሳል። የጉህዴን ሊቀመንበር ዳግም ለእስር መዳረግ በዕርቁ ምክንያት “አንጻራዊ ሰላም” የሰፈነበትን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወደ ግጭት እንዳይከተው የንቅንናቄው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ደርጉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሚፈጸሙ ጥቃቶች በክልሉ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ የሚወነጀለው ጉህዴን፤ እስከ ታህሳስ 2013 ድረስ በህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነት ተደራጅቶ በክልሉ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ነበር። ንቅናቄው በክልሉ ለሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ለመወዳደር ጭምር ዝግጅት ሲያደርግ ቢቆይም፤ ምርጫው ከመካሄዱ አምስት ወራት በፊት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የነበረውን ህጋዊ ዕውቅና አጥቷል።
ጉህዴንን ጨምሮ 28 ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ የተሰረዙት፤ በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ መሰረት “መስፈርቶችን አላሟሉም” በሚል ነው። ይህን ተከትሎ የተወሰኑ የጉህዴን አመራሮች እና አባላት ነፍጥ አንግበው ለመታገል መወሰናቸውን በማስታወቃቸው፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት የንቅናቄውን ከፍተኛ አመራሮችን እና በርካታ አባላት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጎ ነበር።
የክልሉ መንግስት የጉህዴን አመራሮችን ከእስር ከፈታ እና ከንቅናቄው ታጣቂዎች ጋር ዕርቅ ካወረደ በኋላ፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንጻራዊ ሰላም መስፈን ጀምሮ ነበር። ሆኖም ዕርቁን ተከትሎ የጉህዴን ታጣቂዎች ወደ ከተማ እንዲገቡ በመደረጉ በካማሺ ከተማ ዝርፊያዎች መበራከቱን የከተማይቱ ነዋሪዎች እና ኃላፊዎች ከሁለት ወር በፊት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
የካማሺ ዞን የጸጥታ ምክር ቤት ከአስር ቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ፤ በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች “ለማህበረሰቡ ደህንነት ስጋቶች የሚሆኑ እንቅስቃሴዎች” መኖራቸውን ይፋ አድርጓል። በዚህም ምክንያት ከግንቦት 26፤ 2014 ጀምሮ በዞኑ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉን አስታውቋል።
በሰዓት ገደቡ መሰረትም በካማሺ ዞኑ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ ተከልክሏል። በከተማ ውስጥ ሆነ ከከተማ ውጭ በሞተር ሳይክል መንቀሳቀስ እንደማይቻልም የዞኑ ጸጥታ ምክር ገልጿል። እነዚህን ገደቦችን በተላለፈ “ህግ የማያከብር አካል ላይ” የጸጥታ ኃይሎች ለሚወስዱት እርምጃ፤ መንግስት ኃላፊነቱን እንደማይወስድ የዞኑ የጸጥታ ምክር ቤት አስጠንቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)