ሰላም ሚኒስቴር ድጋፍ ለሚሹ ክልሎች ሲያደርገው በቆየው ድጎማ፤ ሶስት ክልሎች አለመካተታቸው አነጋገረ

በሃሚድ አወል

የሰላም ሚኒስቴር ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ድጋፍ ለሚሹ ክልሎች በሚያደርገው አመታዊ የበጀት ድጎማ በሶስት ክልሎች የሚገኙ አርብቶ አደሮች አለመካተታቸው በፓርላማ አነጋገረ። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሶስት ዓመት ወዲህ ሲያደርገው በቆየው ዓመታዊ የ450 ሚሊዮን ብር በጀት ድጎማ ያልተካተቱት በሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ እንዲሁም በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ዞን የሚገኙ አርብቶ አደሮች ናቸው።

ይህ የተገለጸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የሰላም ሚኒስቴርን የ2012/13 በጀት ዓመት የአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር ድጋፍ አሰጣጥ ክዋኔ ኦዲት ሪፖርት መነሻ በማድረግ ትላንት ሰኞ ሰኔ 6፤ 2014 ባካሄደው የህዝብ ውይይት ላይ ነው። በውይይቱ ላይ ከተነሱ ጥያቄዎች አንዱ ለአርብቶ አደሮች የሚሰጠው የድጎማ ድጋፍ ጉዳይ ነው። 

በትላንቱ ውይይቱ ላይ የተገኙት በሰላም ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ካይዳኪ ገዛኸኝ፤ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ መሰረት ለድጎማው የተመረጡት ሶስት ክልሎች ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል። የተመረጡት ክልሎች ጋምቤላ፣ አፋር እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ መሆናቸውንም አስረድተዋል። 

ለበጀት ድጎማው ጋምቤላ፣ አፋር እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ብቻ የተመረጡት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ መሰረት መሆኑን በሰላም ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ካይዳኪ ገዛኸኝ ተናግረዋል | ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

“እነዚያ አካባቢዎች የበጀት እጥረት አለባቸው። የበጀት እጥረት በመኖሩ የሚሰሩት መደበኛ ስራ ነው እንጂ፤ ለህብረተሰቡ ፕሮጀክቶችን እየሰሩ የህብረተሰቡን ህይወት የሚቀይር ነገር የለም። ስለዚህ ቅድሚያ ለእነዚህ ብቻ ይሁን ተብሎ ለእኛ ተሰጠ። ስለዚህ የእኛ [ድርሻ] መፈጸም ብቻ ነው” ሲሉ አቶ ካይዳኪ ሶስቱ ክልሎች የተመረጡበትን ምክንያት አብራርተዋል። 

በፍትህ ሚኒስቴር የፌደራል ህጎች ተፈጻሚነት መከታተያ ዳይሬክቶሬትን በዳይሬክተርነት የሚመሩት ትብለጥ ቡሽራ፤ የተወሰኑ ክልሎችን መርጦ ተጠቃሚ ማድረግ “ምክንያታዊነት የሚጎድለው ነው” ሲሉ ተችተዋል። የበጀት ድጎማው በተደረገባቸው ክልሎችም ጉድለቶች መኖራቸውን በማንሳት ምላሽ እንዲሰጥባቸው ጠይቀዋል። በተለይ በአፋር እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የፕሮጀክት አፈጻጸም እንከን መስተዋሉ በክዋኔ ኦዲት ሪፖርቱ ተመላክቷል። 

በአፋር ክልል ዱብቲ ከተማ የተዘጋጀ 1,500 ሄክታር የእርሻ መሬት ለሁለት ዓመታት ሳይታረስ ጾም ማደሩ ለዚህ እንደ አንድ ማሳያ ተነስቷል። በተመሳሳይ በዚያው በአፋር ክልል ከሰም ስኳር ፕሮጀክት፤ በሳቡሬ የመንደር ማሰባሰብ ማዕከል የተገነቡ 300 መኖሪያ ቤቶች ሰው ሳይገባባቸው መፈራረሳቸው ተጠቅሷል።       

የዱብቲው መሬቱ ሳይታረስ ለመቅረቱ፤ አቶ ካይዳኪ የስኳር ኮርፖሬሽን እና የቀድሞ ውሃ ሀብት ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን ተጠያቂ አድርገዋል። የሰላም ሚኒስትር አማካሪው፤ ሁለቱ ተቋማቱ በአካባቢው መስኖ መገንባት ሲገባቸው ባለመስራታቸው መሬቱ ጾም ማደሩን ገልጸዋል። “ሰብል ማልማት የሚቻለው መስኖ ከተሰራ ነው። መስኖ ስላልተሰራ ማልማት አልተቻለም” ያሉት አቶ ካይዳኪ፤ የሰላም ሚኒስቴር ያደረገው ክትትል “ውጤት ሊያመጣ አለመቻሉን” አክለዋል። 

በከሰም ስኳር ፕሮጀክት የመኖሪያ ቤቶች የተገነቡት ከዘጠኝ ዓመታት በፊት መሆኑን ያስታወሱት የሚኒስትሩ አማካሪ፤ አሁን “ሁሉም ኦና ሆኖ ነው ያለው” ሲሉ በውይይቱ ወቅት የተነሳውን ችግር ዕውነትነት አምነዋል። ችግሩ ያጋጠመው “ጥናት ላይ ተመስርቶ ባለመሰራቱ ምክንያት” መሆኑንም ለውይይቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል። 

ተመሳሳይ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ችግሮች በተስተዋሉበት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲገነባ አራት ሚሊዮን ብር ገደማ ቅድመ ክፍያ የተፈጸመለት ኮንትራክተሩ ስራውን ጥሎ መጥፋቱ በክዋኔ ኦዲት ሪፖርቱ ተጠቅሷል። ጉዳዩን በህግ ለመጠየቅ በተደረገ ጥረትም፤ ኮንትራክተሩ ለባንክ ያስያዘው ቤት የቤተክርስቲያን ይዞታ ሆኖ መገኘቱ ተመላክቷል።

የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አራት ሚሊዮን ብር ገደማ ቅድመ ክፍያ ተፈጽሞለት ያልተገነባን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተመለከተ “ይኼ ቁልጭ ያለ ሙስናን ነው የሚያሳየው” ብለዋል | ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ “ይኼ ቁልጭ ያለ ሙስናን ነው የሚያሳየው” ብለዋል። አቶ ካይዳኪ በበኩላቸው “ጉዳዩ በህግ ተይዟል” የሚል አጠር ያለ ምላሽ ሰጥተዋል። እኒህን መሰል አጭር ምላሾች ግን በውይይቱ ተሳታፊ የሆኑ የሌሎች መስሪያ ቤት ኃላፊዎችን እና ተወካዮችን አላስደሰቱም። 

በተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቤ አራሬ ሞሲሳ “የኦዲት ግኝቱ እና መልሱ ብዙም አይጣጣምም” ሲሉ ጠንከር ያለ አስተያየት ሰጥተዋል። የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተርም “የተመለሰው መልስ አላረካኝም” ሲሉ ተመሳሳይ አስተያየት ሰንዝረዋል። ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዋና ኦዲተር ሆነው በፓርላማ ቃለ መሐላ የፈጸሙት መሰረት፤ “የተመለሰ መልስ ስለሌለ እንደ አዲስ ዕቅድ አውጥተው የዕቅዳቸው አካል አድርገው” እንዲሰሩ ቢደረግ የሚል ሃሳብ አቅርበዋል።

ይህን ተከትሎም የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ፤ አርብቶ አደሮችን የሚመለከት የድጋፍ ስራን ከሰላም ሚኒስቴር ለተረከበው የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር አቅጣጫ ሰጥተዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እስከ ሰኔ 25 ድረስ የድርጊት መርሃ ግብር እንዲያዘጋጅ፤ ተጠያቂነት የሚኖር ከሆነ አስተዳደራዊ ርምጃ እንዲወስድ አቶ ክርስቲያን አሳስበዋል። የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ለአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር የሚደረግን ድጋፍ የማስተባበር ስራን በአዋጅ የተረከበው ከዘጠኝ ወራት በፊት ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)