በጋምቤላ ከተማ የነበረው የተኩስ ልውውጥ “መጠነኛ መረጋጋት” አሳይቷል ተባለ

በተስፋለም ወልደየስ 

የጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ በሆነችው ጋምቤላ ከተማ ዛሬ ማክሰኞ ከንጋት ጀምሮ፤ የጋምቤላ ነጻነት ግንባር እና የሸኔ ወታደሮች “በጋራ ከፍተውት ነበር” የተባለ ተኩስ “መጠነኛ መረጋጋት” ማሳየቱን የክልሉ ፕሬስ ሴክሬተሪያት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የተኩስ ልውውጡ እስከ ረፋድ አራት ሰዓት ድረስ ቀጥሎ እንደነበር ጽህፈት ቤቱ እና የከተማይቱ ነዋሪዎች አረጋግጠዋል። አንድ የአይን እማኝ በበኩላቸው በተኩስ ልውውጡ ጉዳት የደረሰባቸው አራት የጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይል አባላት በሆስፒታል ህክምና ሲደረግላቸው መመልከታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

በጋምቤላ ከተማ የተኩስ ልውውጥ የጀመረው ከጠዋቱ 12:30 ጀምሮ መሆኑን የጋምቤላ ፕሬስ ሴክሬተሪያት ጽህፈት ቤት ዛሬ ማክሰኞ ጠዋት ሰኔ 7 በፌስ ቡክ ገጹ ባወጣው መረጃ አስታውቋል። ጽህፈት ቤቱ የተኩስ ልውውጡ የተካሄደው “በጋምቤላ ከተማ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ለማደፍረስ እየተንቀሳቀሱ” ናቸው ባላቸው “ጸረ ሰላም ኃይሎች” እና በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መካከል መሆኑንም ቀደም ሲል ገልጾ ነበር። ጽህፈት ቤቱ ረፋዱን ባወጣው ተጨማሪ መረጃ ደግሞ “የመንግስት የጸጥታ ኃይል ባካሄደው ብርቱ ትግል ከተማውን በከፊል ነጻ ማውጣት ተችሏል” ብሏል። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሶስት የከተማይቱ ነዋሪዎች ግን የተኩስ ልውውጡ የጀመረው ከንጋቱ 11 ሰዓት ገደማ ጀምሮ እንደነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ተኩሱ ከባድ መሳሪያ ጭምር የተቀላቀለበት እንደሆነ የገለጹት የዓይን እማኞቹ፤ በዚህም ምክንያት አብዛኛው የከተማይቱ ነዋሪ በቤት ውስጥ ተሸሽጎ ሁኔታው እስኪረገብ እየተጠባበቀ እንደሆነ አስረድተዋል። በከተማይቱ የሚሰማው ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ከጠዋቱ አራት ሰዓት በኋላ ረገብ ማለቱንም አክለዋል። 

ከጋምቤላ ከተማ ወደ መቱ በሚወስደው መንገድ አካባቢ እንደሚኖሩ የገለጹ አንድ የዓይን እማኝ፤ የተኩስ ድምጽ ጎልቶ የሚሰማው የባሮ ድልድይን ተሻግሮ እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይል እና የፌደራል ፖሊስ አባላትን በመንገድ ላይ መመልከታቸውን የተናገሩት የዓይን እማኝ፤ የተኩስ ልውውጡን ከመንግስት ጋር እያደረጉ ያሉት ኃይሎች ወደ ከተማው ለመግባት ሙከራ ቢያደርጉም የባሮን ድድልድይ መሻገር እንዳልቻሉ አብራርተዋል። 

የዓይን እማኟ እርሳቸውን ጨምሮ ለመንቀሳቀስ የደፈሩ የከተማይቱ ነዋሪዎች የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ይጠቀሙ እንደነበር አመልክተዋል። በዚህ መልኩ የተጎዱ ሰዎችን ለመመልከት ወደ ጋምቤላ ሆስፒታል መሄዳቸውን የጠቀሱት የአይን እማኟ፤ በዚያም አራት የተጎዱ የጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ህክምና ሲደረግላቸው መመልከታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬተሪያት ጽህፈት ቤት ረፋዱን ባወጣው መግለጫ “በሁለቱም ወገን ላይ ጉዳት መድረሱን” አረጋግጦ፤ ሆኖም “የደረሰው ጉዳት በውል እንደማይታወቅ” ጨምሮ ገልጿል። 

በጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አቅራቢያ የሚኖሩ ሌላ የከተማይቱ ነዋሪ በበኩላቸው፤ ከባድ መሳሪያ የተቀላቀለበት የተኩስ ልውውጥ በቅርበት ርቀት ሲሰሙ መቆየታቸውን ገልጸዋል። በአቅራቢያቸው ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንደማይታይ የገለጹት እኚህ ነዋሪ፤ ሰው በየቤቱ ተሸሽጎ በየቦታው ያለውን ሁኔታ በስልክ እየተከታተለ መሆኑን አስረድተዋል። በእርሳቸው አካባቢ ከንጋት ጀምሮ መብራት በመቋረጡ በሬድዮም ሆነ በሌላ መገናኛ ብዙሃን መረጃ ተላልፎ እንደሆነ ለማወቅ እንደተቸገሩም አክለዋል። 

ዛሬ በጋምቤላ ክልል የተፈጠረውን ሁኔታ በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ ክልሉ የሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ እንዲሁም የክልሉ መንግስት ፕሬስ ሴክሪተሪያት ጽህፈት ቤት በተደጋጋሚ ብንደውልም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)