በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ በ15 ቀን ውስጥ ክስ እንዲመሰረት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተሰጠ

በሃሚድ አወል

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤ በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ ዐቃቤ ህግ በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሰረት ትዕዛዝ ሰጠ። ፍርድ ቤቱ ፖሊስ በጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬ እና መዓዛ መሐመድ ላይ ለሚያደርገው ምርመራ ተጨማሪ አምስት ቀናት ፈቅዷል። 

የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ጉዳይ የያዘው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራውን አጠናቅቆ ለዐቃቤ ህግ ማስተላለፉን ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 7፤ 2014 ለፍርድ ቤቱ በጽሁፍ አስታውቋል። ከፖሊስ የምርመራ መዝገቡን መረከቡን በጽሁፍ ያረጋገጠው ዐቃቤ ህግ የክስ መመስረቻ 15 ቀናት እንዲሰጡት ችሎቱን ጠይቋል።

ዐቃቤ ለችሎቱ ባቀረበው ባለአንድ ገጽ የጊዜ መጠየቂያ ደብዳቤ፤ የወንጀል ምርመራው የሚያተኩርባቸውን “የወንጀል ድርጊቶች” ዘርዝሯል። ተመስገን በዐቃቤ ህግ “ፈጸማቸው” ተብለው ከተዘረዘሩት ወንጀሎች መካከል “የእርስ በእርስ ጦርነት ማነሳሳት” አንደኛው ነው። “ወታደራዊ ምስጢሮችን ለማይመለከተው አካል በግልጽ መጻፍ” ተመስገን የተጠረጠረበት ሌላኛው ወንጀል ነው።

ጋዜጠኛ ተመስገን፤ የመከላከያ ሰራዊት ተቋም ወንጀል ሲፈጸም የማይጠይቅ አስመስሎ በመጻፍ “የተቋሙን እና የሰራዊቱን መልካም ስምና ዝና” አጠልሽቷል ተብሎ ተወንጅሏል። ተመስገን በማኔጂንግ ዳይሬክተርነት በሚመራው ሳምንታዊ የ“ፍትሕ” መጽሔት፤ “የጥላቻ ንግግሮችን” አሰራጭቷል የሚል ውንጀላም በዐቃቤ ህግ ቀርቦበታል። ዐቃቤ ህግ “ጥላቻ የተሞላበት እና ሀሰተኛ” ያላቸውን ጽሁፎችን በማሰራጨት፤ “የሰራዊቱን ሞራል ዝቅ በማድረግ እና እምነቱን ለማፍረስ በተቀናጀ ዘዴ” ተጠርጣሪው ወንጀል መስራቱንም በጽሁፉ አስረድቷል።

ጋዜጠኛ ተመስገንን ወክለው በችሎት የተገኙት ጠበቃው አቶ ሔኖክ አክሊሉ የዐቃቤ ህግን ጥያቄ ተቃውመው፤ ፍርድ ቤቱ የደንበኛቸውን የዋስትና መብት እንዲያስከብርላቸው ጠይቀዋል።  በተመስገን ጉዳይ ለመጀመሪያ ጊዜ ችሎት ፊት ቀርበው የተከራከሩት ዐቃቤ ህግ  የጠበቃውን የዋስትና ጥያቄ ተቃውመዋል፡፡

ዐቃቤ ህጉ የዋስትና ጥያቄውን የተቃወሙት “ ክሳችን ተደራራቢ ሊሆን ስለሚችል [ተጠርጣሪው] በዋስትና ቢወጡ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ” በሚል ምክንያት ነው። ዐቃቤ ህግ ተጠርጣሪው በዋስትና ወጥው “ጉዳት” የሚያደርሱት ማን ላይ እንደሆነ ግን አልገለጹም። የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የጠበቃውን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለዐቃቤ ህግ የክስ መመስረቻ 15 ቀናትን ፈቅዷል። 

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የጋዜጠኛ ተመስገንን ጉዳይ ዛሬ የተመለከተው፤ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የፈቀደው የ10 ሺህ ብር ዋስትና በከፍተኛ ፍርድ ቤት ተሽሮ መዝገቡ አንዲመለስ በመደረጉ ምክንያት ነው። የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዋስትና ትዕዛዙን የሻረው፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በትዕዛዙ ላይ ያቀረበውን ይግባኝ በመቀበል ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]