መስከረም አበራ በዋስትና ከእስር ተለቀቀች

በሃሚድ አወል

“ኢትዮ ንቃት” የተሰኘ የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነችው መስከረም አበራ፤ በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ተለቀቀች። መስከረም ከእስር የተለቀቀችው፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በፍርድ ቤት የተፈቀደላትን የዋስትና መብት አስመልክቶ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረበው ይግባኝ ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 8፤ 2014 ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ነው። 

በምታቀርባቸው የፖለቲካ ትንታኔዎች የበለጠ የምትታወቀው መስከረም፤ ያለፉትን 23 ቀናት በእስር ያሳለፈችው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት ከሚገኘው ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ነበር። መስከረም የዋስትና ሂደቱን አጠናቅቃ ዛሬ ከቀኑ አስራ አንድ ሰዓት ተኩል ገደማ ከፖሊስ ጣቢያው ስትወጣ ቤተሰቦቿ እና ጠበቃዋ ተቀብለዋታል።

መስከረም አበራ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የ30 ሺህ ብር ዋስትና የተፈቀደላት ከትላንት በስቲያ ሰኞ ሰኔ 6፤ 2014 ነበር። ሆኖም የአዲስ አበባ ፖሊስ ሁለት ጊዜ ይግባኝ በማለቱ እስከ ዛሬ ከእስር ሳትፈታ ቆይታለች። 

መርማሪ ፖሊስ የይግባኝ አቤቱታውን ለመጀመሪያ ጊዜ ያቀረበው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነበር። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ይግባኝ ሰሚ ችሎት የፖሊስን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ የመስከረምን ዋስትና ትላንት ማክሰኞ ሰኔ 7፤ 2014 አጽንቷል።

ፖሊስ ትላንት ከሰዓት ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ዳግም የይግባኝ አቤቱታውን ያቀረበ ቢሆንም፤ ለጠየቀው ይግባኝ “ፋይል ባለመደራጀቱ” ጉዳዩ ለዛሬ ረቡዕ ሰኔ 8፤ 2014 ተቀጥሮ ነበር። በዛሬ የሰበር ሰሚ ችሎት ውሎ፤ መርማሪ ፖሊስ እና ዐቃቤ ህግ በተጠርጣሪዋ የዋስትና ጉዳይ ላይ ለክርክር መቅረባቸውን ከመስከረም ጠበቆች አንዱ የሆኑት አቶ ሔኖክ አክሊሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

መርማሪ ፖሊስ “ምርመራዬን ሳልጨርስ የስር ፍርድ ቤቶች ዋስትና ፈቅደዋል” ሲል አቤቱታ ማቅረቡን ጠበቃው ገልጸዋል። ዐቃቤ ህግ በበኩሉ የምርመራ መዝገቡን ከፖሊስ መቀበሉን በመግለጽ ለክስ መመስረቻ 15 ቀናት እንዲሰጡት ችሎቱን መጠየቁንም አክለዋል።

መስከረምን የወከሉት ሁለት ጠበቆች፤ “ዐቃቤ ህግ በስር ፍርድ ቤት ክርክር ሳያደርግ የክስ መመስረቻ ጊዜ መጠይቅ አይችልም” ሲሉ ተከራክረዋል። የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ሰበር ሰሚ ችሎቱ “ጉዳዩ አያስቀርብም፤ ዐቃቤ ህግም [በችሎቱ] ሊስተናገድ የሚችልበት የህግ አግባብ የለም” በሚል የመስከረምን ዋስትና ማጽናቱን አቶ ሔኖክ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።

መስከረም አበራ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለችው ከ23 ቀን በፊት ግንቦት 13፤ 2014 ነበር። ፖሊስ በመስከረም ላይ ምርመራ ሲያካሄድ የቆየው “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት” ወንጀል ስለጠረጠራት እንደሆነ ለፍርድ ቤት በተደጋጋሚ ማስታወቁ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)