በሃሚድ አወል
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ ላይ ተጨማሪ የሰባት ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ። ችሎቱ የምርመራ ጊዜውን የፈቀደው ፖሊስ “በምርመራው የሚያጠናቅቃቸው ነገሮች ካሉ” በሚል ነው።
ያየሰው ዛሬ ሰኞ ሰኔ 6፤ 2014 ችሎት ፊት የቀረበው ያለጠበቃ ነበር። ጠበቃው ሌላ ችሎት እንዳላቸው ለፍርድ ቤቱ የገለጸው ጋዜጠኛው፤ ጉዳዩ ከሰዓት እንዲታይለት ችሎቱን ጠይቋል። የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ዳኛ በበኩላቸው “ከሰዓት ሌላ ቀጠሮ አለን” በማለት የያሰውን ጥያቄ ሳይቀበሉት ቀርተዋል።
ዳኛው “ጠበቃው እስከ ስድስት ሰዓት የሚደርሱ ከሆነ እንጠብቃለን” ቢሉም፤ ያየሰው ጠበቃው መድረስ እንደማይችሉ በመግለጽ ራሱ ተከራክሯል። ላለፉት 19 ቀናት በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛው፤ ችሎቱ የዋስትና መብቱን እንዲጠብቅለት ጠይቋል። የፖሊስን የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እና የያሰውን የዋስትና ጥያቄዎች ያደመጠው ችሎቱ፤ በስተመጨረሻ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የያሰውን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ያደረገው ፍርድ ቤቱ፤ ፖሊስ ከጠየቀው የምርምራ ጊዜ ግማሹን ፈቅዷል። በጋዜጠኛ ያየሰው ላይ የምርመራ ጊዜ ሲፈቀድ ይህ ለሶስተኛ ጊዜ ነው። ያየሰው ከ18 ቀናት በፊት ግንቦት 19፤ 2014 ለመጀመሪያ ጊዜ ችሎት በቀረበበት ወቅት ለፖሊስ 10 የምርመራ ቀናት ተፈቅደውለት ነበር። በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ግንቦት 30 ለፖሊስ ስድስት ቀናት ተፈቅዶለታል። ያየሰው የዛሬውን ጨምሮ ለአራት ጊዜያት ያህል ችሎት ፊት ቀርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)