በጸጥታ ችግሮች ምክንያት ለኢንዱስትሪዎች ለማቅረብ የታቀደው የጥጥ መጠን ከግማሽ በታች መቀነሱ ተነገረ

በሃሚድ አወል

ባለፉት አስር ወራት ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ለማቅረብ ከታቀደው 35 ሺህ ቶን ጥጥ ውስጥ ማሳካት የተቻለው ከግማሽ በታች መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ። በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ “የጸጥታ ችግሮች”፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥጥን ጨምሮ ሌሎች ግብዓቶችን ባቀደው ልክ ለኢንዱስትሪዎች እንዳያቀርብ ምክንያት እንደሆነበት ገልጿል። 

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይህን የገለጸው የመስሪያ ቤቱን የአስር ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትላንት ሐሙስ ሰኔ 9፤ 2014 ባቀረበበት ወቅት ነው። አሁን በስራ ላይ ያሉት አምራች ኢንዱስትሪዎች እየገጠማቸው ካለው ችግር ውስጥ 55 በመቶ የሚሆነው ከግብዓት አቅርቦት ጋር የተያያዘ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል።  

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ይህ የግብዓት አቅርቦት ችግር የተፈጠረው በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የግብርና እና የማዕድን ጥሬ ዕቃዎች “በመጠን፣ በአይነት እና በጥራት በቂ” ባለመሆናቸው ምክንያት እንደሆነ ሚኒስትሩ አስረድተዋል። ከውጭ ምንዛሬ ጋር በተያያዘም የግብዓት አቅርቦት ችግሮች እንደሚታዩ አቶ መላኩ ጨምረው ገልጸዋል።

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሪፖርት መሰረት ከፍተኛው የግብዓት አቅርቦት ችግር ያጋጠመው በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ላይ ነው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለእነዚህ ኢንዱስትሪዎች በግብዓትነት የሚያገለግል 35 ሺህ ቶን ጥጥ ከሀገር ውስጥ ለመሰብሰብ እና ለማቅረብ አቅዶ እንደነበር የጠቀሱት አቶ መላኩ፤ ሆኖም ባለፉት 10 ወራት ማቅረብ የቻለው 15.6 ሺህ ቶን የተዳመጠ ጥጥ ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል።  

ለአቅርቦቱ ማነስ ዋነኛ ምክንያት የሆነው “በአንዳንድ ጥጥ አብቃይ አካባቢዎች የነበሩ የጸጥታ ችግሮች” መሆኑን ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላት በንባብ ባቀረቡት ባለ 15 ገጽ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ አመልክተዋል። ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ጥጥን ጨምሮ ሌሎችንም ጥሬ ዕቃዎችን “ማግኘት የምንችልበት ሁኔታ አልነበረም” ሲሉ አቶ መላኩ ሁኔታውን አብራርተዋል። የዘንድሮው የበጀት ዓመቱ በሚጠናቀቅበት ወር ላይ ሪፖርታቸውን ያቀረቡት ሚኒስትሩ፤ “በአንዳንድ ጥጥ አብቃይ አካባቢዎች የነበሩ የጸጥታ ችግሮች ለአቅርቦቱ ማነስ ያሳደሩትን ጫና በመቋቋም ቀሪውን ጥጥ ለፋብሪካዎች ለማቅረብ እየተሰራ ይገኛል” ብለዋል። 

ፎቶ፦ ከሲ. ኤን. ኤን የቪዲዮ ዘገባ የተወሰደ

እንደ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ሁሉ የምግብ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎችም ተመሳሳይ የግብዓት አቅርቦት ችግር እንደገጠማቸው አቶ መላኩ ተናግረዋል። “የእኛ ኢንዱስትሪዎች አሁን ያላቸውን የማምረት አቅም ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም የሚያስችል ግብዓት በሀገር ውስጥ እየተመረተ አይደለም” ሲሉ የችግሩን መንስኤ ለፓርላማ አባላት ያስረዱት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ፤ ለግብዓት በሚሆኑ ምርቶች “የሚሸፈነው የመሬት መጠንም አነስተኛ ነው” ሲሉ ችግሩ መሰረታዊ መሆኑን አብራርተዋል። ለትልልቅ እና ትንንሽ እርሻዎች የሚደረገው ድጋፍ “ውስንነት ያለበት” መሆኑ ባለሃብቶች በግብዓት ምርት ላይ እንዳይሰማሩ እንዳደረጋቸውም ጠቁመዋል።  

የምግብ ዘይት ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጓቸው ግብዓቶች በሀገር ውስጥ አቅርቦት መሸፈን ባይቻልም፤ ከውጪ ለሚያስመጧቸው ግብዓቶች ቅድሚያ ትኩረት ካገኙ ዘርፎች ውስጥ እንዲካተቱ መደረጋቸውን አቶ መላኩ ገልጸዋል። ባለፉት 10 ወራት ብቻ የፓልም ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች ለግብዓት መግዣ 201.6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማግኘታቸውን ሚኒስትሩ ለዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል። 

ከጨርቃ ጨርቅ እና የምግብ ዘይት ኢንዱስትሪዎች ሌላ በታቀደው ልክ ባለፉት 10 ወራት ግብዓት ያልቀረበላቸው የቆዳ እና የቆዳ ውጤት አምራች ኢንዱስትሪዎች መሆናቸው ለፓርላማ በቀረበው ሪፖርት ላይ ሰፍሯል። የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለቆዳ እና የቆዳ ውጤት አምራች ኢንዱስትሪዎች ለማቅረብ ካቀደው የቆዳ እና ሌጦ ምርት ያቀረበው 67 በመቶውን ብቻ ነው። ለዚህም ምክንያቱ “የዓለም አቀፍ የቆዳ ምርቶች ገበያ መቀዛቀዝ ጋር ተያይዞ በሀገር ውስጥ ያሉ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች የጥሬ ዕቃ ፍላጎት በመቀነሱ” መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የግብዓት አቅርቦት ችግር በኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል ተብሏል። በኢትዮጵያ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ከማምረት አቅማቸው ውስጥ ባለፉት 10 ወራት ውስጥ መጠቀም የቻሉት 49.2 በመቶውን ብቻ መሆኑን አቶ መላኩ በሪፖርታቸው ይፋ አድርገዋል። ከሌሎች የኢንዱስትሪ ዘርፎች ጋር ሲነጻጸር በማምረት አቅም ዝቅተኛ አፈጻጸም ያሳየው የማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ እና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ነው። ዘርፉ ካለው የማምረት አቅም ባለፉት 10 ወራት ጥቅም ላይ ያዋለው 23.1 በመቶ ብቻ መሆኑ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሪፖርት ተገልጿል። 

በማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ እና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ የታየው የማምረት አቅም ማነስ ዋነኛ ምክንያት የግብዓት አቅርቦት ችግር መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል። ዘርፉ ያለውን የማምረት አቅም መጠቀም ያልቻለው “ለከፍተኛ ማሽነሪዎች የሚያስፈልጉ የብረት አቅርቦቶች በበቂ መጠን ባለመገኘታቸው” መሆኑን አቶ መላኩ በማብራሪያቸው ላይ አንስተዋል። የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይህንን ዘርፍ ጨምሮ በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የተስተዋሉ የአቅርቦት ችግሮችን ለመቅረፍ የመፍትሔ እርምጃዎችን ቢወስድም፤ “በታሰበው ልክ” ውጤት አለማምጣቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አምነዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)