የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ሰኞ ሰኔ 13 ሊወያይ ነው። የህብረቱ የውጪ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል በሊቀመንበርነት የሚመሩት የዛሬው ስብሰባ፤ በሶማሊያ ወቅታዊ ሁኔታ እና በሱዳን ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ላይ የሚወያይ ቢሆንም የኢትዮጵያ ጉዳይም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል።
በሉግዘምበርግ በሚካሄደው በዚሁ የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ጉዳይ በአጀንዳነት የተያዘው፤ በአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ጉዳዮች ስር ነው። የአውሮፓ ካውንስል ለዚሁ ስብሰባ ያዘጋጀው እና “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ ሁኔታ “የተወሰነ መሻሻል” እንደታየበት ቢጠቅስም አሁንም ተግባራዊ ሊደረጉ የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ጠቁሟል። ዘላቂ የተኩስ አቁም፣ የኤርትራ ወታደሮች መውጣት፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች የፈጸሙን ተጠያቂ በማድረግ ረገድ መሳካት የሚኖርባቸው በርካታ ጉዳዮች እንደሚቀሩ በዚሁ ሰነድ ላይ ሰፍሯል።
በዛሬው ስብሰባ ላይ የህብረቱ የሰብዓዊ መብቶች ልዩ መልዕክተኛ ኤይሞን ጊልሞር ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የዲፕሎማቲክ ምንጮች ገልጸዋል። ልዩ መልዕክተኛው ባለፈው ወር ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው ከፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር መገናኘታቸው ይታወሳል።
አይርላንዳዊው ዲፕሎማት በአዲስ አበባው ቆይታቸው በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ ያጠነጠኑ ውይይቶች ማድረጋቸው ተነግሮ ነበር። ልዩ መልዕክተኛው ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ እና ከፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ጋር በነበራቸው ውይይቶች፤ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች እና የዓለም አቀፍ ህግ ጥሰቶች ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ላይ አጽንኦት መስጠታቸውን በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ በወቅቱ ገልጸዋል።
የልዩ መልዕክተኛው የግንቦቱ ጉብኝት፤ የዩክሬን እና የሩሲያ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በአውሮፓ ህብረት ቸል የተባለው የኢትዮጵያ ጉዳይ ከሰሞኑ መልሶ ወደ መነጋገሪያ አጀንዳነት መምጣቱን ያመላከተ ነበር። የአውሮፓ ህብረት እንደ ኤይሞን ጊልሞር ያሉ ዲፕሎማቶችን ወደ አዲስ አበባ ከመላክ ባሻገር፤ የኢትዮጵያ ባለስልጣናትንም የህብረቱ መቀመጫ በሆነችው ብራስልስ ተቀብሎ አነጋግሯል።
ወደ ብራስልስ ያቀኑት የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ከህብረቱ የሰብዓዊ መብት ልዩ መልዕክተኛ እንዲሁም ከአውሮፓ ህብረት የቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ያኔዝ ሌናርቺች ጋር ተወያይተዋል። ኤይሞን ጊልሞር ከዶ/ር ጌዲዮን ለሁለተኛ ጊዜ ከተገናኙ በኋላ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመመርመር ያቋቋመውን የባለሙያዎች ቡድን ጉዳይ ጠቀስ አድርገዋል።
ዶ/ር ጌዲዮን በጄኔቫ ስለነበራቸው ውይይት ገለጻ እንዳደረጉላቸው የገለጹት ጊልሞር፤ ይህ ውይይት በኢትዮጵያ በነበረው ግጭት ሳቢያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን መመርመር ያስችለው ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳጫረባቸው ገልጸዋል። ዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ኮሚሽን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተቋቋመው በየካቲት 2014 ቢሆንም በኢትዮጵያ በኩል እስካሁን በይፋ ተቀባይነት አላገኘም።
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሰኔ 8 በተካሄደው የዶ/ር ጌዲዮን እና የሌናርቺች ውይይት የተነሳው ዋነኛ ጉዳይ ደግሞ “በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ” እንደነበር በወቅቱ የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል። በውይይቱ አጽንኦት ከተሰጠባቸው ጉዳዮች ውስጥ፤ በትግራይ እና የተቸገሩ ሰዎች ባሉባቸው በየትኞቹም የኢትዮጵያ ክልሎች “የተሟላ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲቀርብ የመፍቀድ አስፈላጊነት” እንደሚገኝበት ተገልጿል።
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የዛሬ ስብሰባ የኢትዮጵያን ቀውስ ለመፍታት ግፊት ከማድረግ ባሻገር ህብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖረውን የወደፊት ግንኙነት የሚገመግምበት እንደሚሆን አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ዲፕሎማት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የዩክሬን ጦርነት መቀስቀስ ህብረቱ ለኢትዮጵያ የነበረውን ትኩረት እንዳናጠበው የጠቀሱት ዲፕሎማቱ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መዘዝ የሻከረውን ግንኙነት ለማደስ በርካታ የቤት ሥራዎች እንዳሉ ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)