ብሪታኒያ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባህር ቀጠና የምታራምደውን ፖሊሲ በኃላፊነት የሚመሩ አዲስ ልዩ ልዑክ ሾመች። በቀይ ባህር ቀጠና የሚንቀሳቀሱ የውጭ ኃይሎች የሚያከናውኗቸውን ጥረቶች ከብሪታንያ ምላሽ ጋር የማቀናጀት ሚና ላለው ለዚህ ኃላፊነት የተሾሙት ሳራ ሞንትጎሜሪ የተባሉ ዲፕሎማት ናቸው።
የዲፕሎማቷን ሹመት ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 14 ይፋ ያደረገው የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ነው። አዲሲቷ ተሿሚ ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ የብሪታንያ ልዩ ልዑክ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩትን ፊሊፕ ፓራምን የሚተኩ ናቸው።
ላለፉት 15 ዓመታት በብሪታንያ መንግስት ስራ ላይ የቆዩት ሳራ ሞንትጎሜሪ፤ ኬንያን ጨምሮ በተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በኃላፊነት ቦታዎች ተመድበው አገልግለዋል። ሳራ በኬንያ ቆይታቸው የብሪታንያ ዓለም አቀፍ ልማት ተቋም ቅርንጫፍ መስሪያ ቤትን ለሁለት ዓመት በኃላፊነት መርተዋል። የአሁኑን የልዩ ልዑክ ኃላፊነት ከመረከባቸው አስቀድሞ ደግሞ አሜሪካ በሚገኘው የብሪታንያ ኤምባሲ የንግድ እና ኢኮኖሚ ካውንሰለር ሆነው ሰርተዋል።
![](https://ethiopiainsider.com/wp-content/uploads/2022/06/Sarah-Montogomery-.jpg)
ብሪታንያ ከቀይ ባህር ቀጠና ጋር ያላት ግንኙነት “በወሳኝ ወቅት ላይ” እንደሚገኝ የጠቆሙት በሀገሪቱ የውጭ፣ የጋራ ብልጽግና እና ልማት ቢሮ የአፍሪካ ሚኒስትር የሆኑት ቪኪ ፎርድ፤ የሳራ በቦታው ላይ መሾም ብሪታንያ ከቀጠናው ጋር ያላትን ግንኙነት በመጪዎቹ ዓመታት “ወደፊት እንደሚያራምደው” እምነታቸውን ገልጸዋል። ሚኒስትሯ አዲሲቷን ተሿሚ “ልምድ ያላት ዲፕሎማት” ሲሉ ገልጸዋታል።
ብሪታንያ ሰብዓዊ ቀውስ ላየለበት የአፍሪካ ቀንድ እና “የጠበቀ ትስስር” አለኝ የምትላቸውን የባህረ ሰላጤው አገራትን በቀጥታ ለሚመለከተው የቀይ ባህር ቀጠና ልዩ ልዑክ ስትሾም በአራት ዓመት ውስጥ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው። ከብሪታንያ በዓመታት ዘግይታ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሾመችው አሜሪካ በአንድ ዓመት ገደማ ውስጥ ሶስት ዲፕሎማቶችን ቀያይራለች።
አለመረጋጋት ለበረታበት የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና፤ የአሜሪካ ተገዳዳሪ ቻይናም ተቀራራቢ ኃላፊነት የተሰጣቸው ዲፕሎማት ሰይማለች። ባለፈው የካቲት አጋማሽ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ሆነው የተሾሙት ሸዌ ቢንግ፤ በአዲስ አበባ በተጀመረው የቻይና የሰላም ጉባኤ ላይ በቀጠናው የሚታዩ ውዝግቦችን ለመሸምገል ግብዣ ማቅረባቸውን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ከብሪታንያ፣ አሜሪካ እና ቻይና በተጨማሪ፤ የአውሮፓ ህብረት እና ፈረንሳይ የየራሳቸውን ልዩ መልዕክተኛ ለአፍሪካ ቀንድ መድበዋል። የአውሮፓ ህብረት እና የፈረንሳይ ልዩ ልዑካን ወደ አዲስ አበባ እና ካርቱም በመመላለስ በቀጠናው ለሚታየው ፖለቲካዊ እና የጸጥታ ቀውስ መፍትሔ ለማፈላለግ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
የእነዚህን ዲፕሎማቶች ጥረት ከሀገራቸው ፖሊሲ ጋር የማጣጣም እና የማቀናጀት ኃላፊነት የተጣለባቸው ሳራ ሞንትጎሜሪ፤ ለቀጠናው “ወሳኝ” በሆነው በዚህ ጊዜ በቦታው በመሾማቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። የአፍሪካ ቀንድ፤ “በግጭት፣ አለመረጋጋት እና ከከባድ የአየር ሁኔታ ክስተቶች” ጋር በተያያዘ ሰብዓዊ ቀውስ እንደተጋረጠበት የገለጹት አዲሲቷ ተሿሚ፤ በዚህ ላይ በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ሳቢያ የተከሰተው የዓለም አቀፍ የምግብ ዋጋ መናር በቀጠናው የሚገኘውን በርካታ ቁጥር ያለው ህዝብ “ወደ ረሃብ እየገፉው” መሆኑን ገልጸዋል። እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ከብሪታንያ የአካባቢው እና አለም አቀፍ አጋሮች ጋር ለመስራት ዕቅድ እንዳላቸውም ሹመታቸው ይፋ በሆነበት መግለጫ ጠቅሰዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)