በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ ክስ ተመሰረተ

የሳምንታዊው “ፍትሕ” መጽሄት ማኔጂንግ ዳይሬክተር በሆነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 21 መደበኛ ክስ ተመሰረተ። ዐቃቤ ህግ በተመስገን ላይ የክስ መዝገብ የከፈተው፤ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የህግ መንግስት እና የሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት መሆኑን ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ከግንቦት 18 ጀምሮ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት በሚገኝበት ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ የሚገኘው ጋዜጠኛ ተመስገን ዛሬ ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቢወሰድም፤ “ዳኛ የለም” በመባሉ በችሎት ፊት ሳይቀርብ ቀርቷል። “ዳኛ ስለሌለ የክስ ቻርጁም አልደረሰንም። ነገ ጠዋት ይዘነው እንመጣለን ብለው ተመልሰዋል” ሲሉ አቶ ሄኖክ ዛሬ ከሰዓት በከፍተኛው ፍርድ ቤት የነበረውን ሁኔታ አስረድተዋል።

የጋዜጠኛው ጠበቃ በደንበኛቸው ላይ መደበኛ ክስ መመስረቱን ቢያረጋግጡም፤ ዝርዝር ነገሩ ምን እንደሆነ እንዳልተገለጸላቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ተመስገን ደሳለኝ በቁጥጥር ስር የዋለው “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት” ተጠርጥሮ መሆኑን ፖሊስ በመጀመሪያዎቹ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ወቅቶች ሲገልጽ ቢቆይም፤ ዐቃቤ ህግ ግን በስተኋላ ላይ ጋዜጠኛው “የእርስ በእርስ ጦርነት በማነሳሳት” ጭምር እንደሚጠረጠር ለፍርድ ቤት ገልጾ ነበር። 

ዐቃቤ ህግ በተመስገን ላይ የክስ መመስረቻ ጊዜ እንዲሰጠው ሰኔ 7፤ 2014 ለፍርድ ቤት ባስገባው ማመልከቻ ላይ፤ ተመስገን “ወታደራዊ ምስጢሮችን ለማይመለከተው አካል በግልጽ በመጻፍ” ወንጀል እንደተጠረጠረ በተጨማሪነት ጠቅሶ ነበር። የመከላከያ ሰራዊት ተቋም ወንጀል ሲፈጸም የማይጠይቅ አስመስሎ በመጻፍ “የተቋሙን እና የሰራዊቱን መልካም ስምና ዝና አጠልሽቷል” በሚል በዐቃቤ ህግ ማመልከቻ የተወነጀለው ተመስገን፤ “የሰራዊቱን ሞራል ዝቅ በማድረግ እና እምነቱን ለማፍረስ በተቀናጀ ዘዴ” ወንጀል በመስራት መጠርጠሩም በወቅቱ ተገልጿል።

ይህ ማመልከቻ የቀረበለት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤ ዐቃቤ ህግ በተመስገን ደሳለኝ ላይ በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሰረት ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል። የፌደራል ዐቃቤ ህግ የተሰጠው ቀነ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት ዛሬ መደበኛ ክስ መመስረቱ ታውቋል። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)