በተስፋለም ወልደየስ
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ “ወታደራዊ ሚስጥሮችን ላልተፈቀደለት ሰው ወይም ለህዝብ በመግለጽ”፣ “የሀሰት ወይም የሚያደናግር መረጃ በማሰራጨት” እንዲሁም “መገፋፋት እና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር” በመፈጸም ወንጀሎች ተከሰሰ። የፌደራል ዐቃቤ ህግ በተመስገን ላይ ያቀረበው የክስ ዝርዝር ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 22፤ 2014 በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተነብቧል።
ዐቃቤ ህግ በጋዜጠኛው ላይ ክስ የመሰረተው በትላንትናው ዕለት ቢሆንም፤ የክስ መዝገብ በተከፈተበት የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የህግ መንግስት እና የሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት “ዳኛ የለም” በመባሉ ጉዳዩ ለዛሬ ጠዋት ተቀጥሮ ነበር። ዛሬ ረፋዱን በተሰየመው ችሎት፤ በ“ፍትሕ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ላይ የቀረበው ክስ በንባብ የተሰማ ሲሆን፤ በጋዜጠኛው ጠበቃ በኩል የተነሳው የዋስትና ጥያቄም ተደምጦበታል።

በጋዜጠኛ ተመስገን ላይ የቀረበው የመጀመሪያው ክስ በኢፌዲሪ የወንጀል ህግ “ወታደራዊ ምስጢርን መግለጽ” በተመለከተ የተደነገገውን አንቀጽ ተላልፏል በሚል የቀረበ ነው። በተከሳሹ ላይ የተጠቀሰበት የወንጀል ህጉ አንቀጽ “ማንኛውም ሰው በጠቅላላው በሕዝብ ዘንድ ያልታወቁትንና በጠባያቸው ከፍተኛ ቁም ነገር በመያዛቸው ምክንያት ላልተፈቀደለት ሰው ወይም ለሕዝብ እንዳይገለጹ በምስጢር የሚጠበቁትን ወታደራዊ ምስጢርነት ያላቸውን ማናቸውንም ዓይነት ሰነዶች ወይም መረጃዎች ላልተፈቀደለት ሰው ወይም ለህዝብ መግለጽ ወይም ማስተላለፍ” ይከለክላል።
ተመስገን ደሳለኝ ይህን የወንጀል ህግ አንቀጽ በመተላለፍ፤ “በሀገሪቱ ከፍተኛ የፖለቲካ እና የጦር አመራሮች መሀል የተደረገ ሚስጥራዊ ውይይት እና የሃገሪቱን የጦር ኃይል መሳሪያ አቅም ለህዝብ እና ላልተገቡ አካላት እንዲገለጽ በማድረግ” ወንጀል መከሰሱን ዐቃቤ ህግ በክስ ቻርጁ ላይ አስፍሯል። ከሳሽ ዐቃቤ ህግ ለዚህ ውንጀላው በማስረጃነት ያቀረበው፤ ተመስገን በስራ አስኪያጅነት ይመራዋል ባለው በልህቀት ኮሚኒኬሽን ብሮድካስት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስር በሚታተመው “ፍትሕ” መጽሔት ላይ የወጡ አራት ጽሁፎችን ነው።
ከአራቱ ጽሁፎች መካከል በ“ፍትሕ” መጽሔት ባለፈው የካቲት 2014 ታትሞ የወጣው የብርጋዴየር ጄነራል ተፈራ ማሞ ቃለ ምልልስ ይገኝበታል። “የጄነራሉ ሚስጥሮች” በሚል ርዕስ ስር በመጽሔቱ በተስተናገደው በዚህ ቃል ምልልስ፤ ተመስገን “ጄነራሉ የነገሩትን ወታደራዊ ሚስጥሮች ለህዝብ ለማሳወቅ በማሰብ”፤ “በሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ህወሓት መካከል ስለነበረው ውጊያ፤ ወታደራዊ አመራሮች የተለዋወጡትን ሚስጥራዊ ንግግሮች እና ግምገማዎች በእትሙ ላይ እንዲገለጽ አድርጓል” በሚል ዐቃቤ ህግ ከስሷል።

በጋዜጠኛ ተመስገን የመጀመሪያ ክስ ላይ በማስረጃነት ከተጠቀሱ ጽሁፎች ውስጥ ሁለቱ፤ ከሶስት ዓመት በፊት በ2011 በ “ፍትሕ” መጽሔት ላይ ለንባብ የበቁ ናቸው። ተመስገን “ሪፎርም ወይስ ፈረቃ” በሚል ርዕስ ስር በመጋቢት 2011 በታተመ ጽሁፍ፤ “ለማንም ሊገለጽ የማይገባ ሀገራዊ ወታደራዊ ቁመና ከሌሎች ሀገራት ወታደራዊ አቋም ጋር በማነጻጸር ለህዝብ ገልጿል” በሚል ተወንጅሏል።
ሌላው በ2011 የታተመ ጽሁፍ እና በተከሳሹ ላይ በማስረጃነት የቀረበው ጽሁፍ “ወታደራዊ አመፅ ያሰጋል” በሚል ርዕስ ስር የወጣ መሆኑ ተጠቅሷል። “ሰነዱ ከመከላከያ የተገኘው እንኳን ቢሆን ሃገራዊ ሚስጥር በመሆኑ ለማንም ሊገለጽ የማይገባ በመሆኑ በሚስጥር መያዝ ሲገባው ከመከላከያ የተገኘ ሰነድ በማለት ወታደራዊ ቁመና ግምገማ እና ሪፖርት የሚያሳይ ሰነድ 19 ገጽ በማለት ይዘቶቹን በመቀነጫጨብ አሳማኝ ሆኖ እንዲገኝ ለማድረግ የሃገር መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም ጽህፈት ቤት የሚል ማህተም ተመቶበታል ብሎ በመጻፍ በእትሙ ገልጿል” በሚል ዐቃቤ ህግ በክስ ቻርጁ ላይ አትቷል።
በጋዜጠኛ ተመስገን ላይ የቀረበው ሁለተኛ ክስ “የሀሰት ወይም የሚያደናግር መረጃ አሰራጭቷል” የሚል ነው። ዐቃቤ ህግ ይህንን በተመለከተ በኢፌዲሪ የወንጀል ህግ ከሰፈረው ድንጋጌ ውስጥ “ወታደሮች ከስነ ስርዓት ውጭ እንዲሆኑ፣ እንዳይታዘዙ ለማነሳሳት ወይም በህዝቡ መካከል አለመረጋጋትና ሁከት እንዲነሳ ለማበረታት በማሰብ የሀሰት ወሬዎችን መንዛት እና ማሰራጨት” የሚለውን ወንጀል ነጥሎ በማውጣት ተመስገንን ተጠያቂ አድርጎታል።

በዐቃቤ ህግ የክስ ቻርጅ ላይ ለዚህ በማስረጃነት የቀረቡት በ“ፍትሕ” መጽሔት በተለያዩ ጊዜያት የወጡ አምስት ጽሁፎች ናቸው። በመጀመሪያው ክስ የተጠቀሱት “ሪፎርም ወይስ ፈረቃ” እና “የጄነራሉ ሚስጥሮች” በሚሉ አርዕስቶች የታተሙ ጽሁፎች በሁለተኛው ክስ ላይም በማጣቀሻነት ቀርበዋል። “መከላከያ ሰራዊት እና የሹም ዘብ”፣ “ወታደራዊ ጉዳዮች” እና “መከላከያ ተቋማዊ ወይስ ኔትዎርክ” በሚሉ አርዕስቶች በ2011፣ በ2012 እና በ2014 በ“ፍትሕ” መጽሔት የታተሙ ሶስት ጽሁፎችም በተመሳሳይ መልኩ ወንጀሉን የሚያስረዱ ናቸው በሚል በክስ ቻርጁ ላይ ተጠቅሰዋል።
በ“ፍትሕ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ላይ በሶስተኛነት የቀረበው ክስ “መገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት የወንጀል ተግባር” ፈጽሟል የሚል ነው። ተመስገን ደሳለኝ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ክስ ቀርቦበት የሶስት ዓመት እስራት ከተበየነበት በኋላ በዝዋይ ማረሚያ ቤት እስሩን ጨርሶ ወጥቷል። በአሁኑ ክስ ተመስገን የተወነጀለው “የህዝቡን ሞራል ዝቅ ለማድረግ፣ እምነቱን ወይም የመቋቋም ኃይሉን በተቀናጀ ዘዴ ለማፍረስ በማሰብ” በ“ፍትሕ” መጽሔት የተለያዩ እትሞች ላይ ስምንት ጹሁፎችን እንዲሰራጭ በማድረግ ነው።
በመጀመሪያው እና ሁለተኛው ክስ ላይ የተጠቀሰው የብርጋዴየር ጄነራል ተፈራ ማሞ ቃለ ምልልስ በሶስተኛው ክስ ላይም በማስረጃነት በድጋሚ ቀርቧል። በማስረጃነት የቀረቡት ቀሪዎቹ ሰባት ጽሁፎችም፤ በቀደሙት ሁለት ክሶች ላይ የተጠቀሱ ናቸው። ጹሁፎቹ ከመጋቢት 2011 ተመስገን ከመታሰሩ ሁለት ወር በፊት በየካቲት 2014 በ“ፍትሕ” መጽሔት ለንባብ የቀረቡ ናቸው።
ጋዜጠኛው በእነዚህ ጽሁፎች “ ትክክለኛ ያልሆነ፣ ጥላቻ የተሞላበት ወይም ህዝብ ያለውን አቋም የሚያፈርስ መረጃ በተቀናጀ ዘዴ በተከታታይ እትሞች ለህዝብ እንዲሰራጭ አድርጓል” በሚል በዐቃቤ ህግ ተከስሷል። ተመስገን በዚህኛው ክስ ጥፋተኛ ሆኖ ቢገኝ በቀላል እስራት አሊያም ወንጀሉ ከባድ ከሆነ ከአስር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ሊቀጣ እንደሚችል በኢፌዲሪ የወንጀል ህግ ላይ ተደንግጓል።
“የሀሰት ወይም የሚያደናግር መረጃ ማሰራጨት” የሚለው ወንጀልም በተመሳሳይ ከአስር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ በወንጀል ህጉ ላይ ሰፍሯል። ሆኖም ወንጀሉ ከባድ ከሆነ ቅጣቱ እስከ ዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ሊደርስ እንደሚችልም በህጉ ላይ ተቀምጧል። “ወታደራዊ ምስጢርን መግለጽ” በተመለከተ በተመስገን ላይ በክስ ቻርጁ የተጠቀሰው አንቀጽ በበኩሉ ከአምስት ዓመት የማያንስ ጽኑ እስራትን የሚያስከትል ነው።
በዛሬው የችሎት ውሎ የተመስገን ደሳለኝ ጠበቃ የሆኑት አቶ ሄኖክ አክሊሉ የደንበኛቸው የዋስትና መብት እንዲጠበቅ ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርበዋል። የፌደራል ዐቃቤ ህግም በጋዜጠኛው ጠበቃ የቀረበውን የዋስትና ጥያቄ በመቃወም መከራከሪያውን ለችሎቱ አሰምቷል። የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤቱ በዋስትናው ጥያቄ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለነገ በስቲያ አርብ ሰኔ 24፤ 2014 ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)