ለአምስት አዲስ የኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያ ሞገዶች ጨረታ ወጣ

በተስፋለም ወልደየስ

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በአዲስ አበባ ከተማ ለሚሰራጩ አዲስ የኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያዎች የሚሆኑ አምስት ሞገዶችን ለጨረታ አቀረበ። በዚህ ጨረታ አማካኝነት ተወዳድረው የሚያሸንፉ አመልካቾች ለስድስት ዓመት ጸንቶ የሚቆይ እና ከዚያ በኋላ በየጊዜው የሚታደስ ፍቃድ ያገኛሉ ተብሏል። 

በኢትዮጵያ ለሚሰራጩ ማንኛውም አይነት የብሮድካስት አገልግሎቶች ፈቃድ የመስጠት ስልጣን በአዋጅ የተሰጠው ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ጨረታውን ያወጣው ባለፈው እሁድ ሰኔ 19፤ 2014 ነው። በመስሪያ ቤቱ አማካኝነት ለአገልግሎት ዝግጁ የሆኑት የሬድዮ ሞገዶች በ92.5፣ 93.5፣ 94.5፣ 95.5 እና 96.5 ሜጋ ኸርዝ ላይ የሚገኙ ናቸው።    

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ኢድሪስ በአሁኑ ጨረታ መስሪያ ቤታቸው ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ለፕሮጀክት ጥናት ሰነድ መሆኑን ተናግረዋል

እነዚህን የሬድዮ ሞገዶች ተጠቅመው የኤፍ ኤም የሬድዮ ጣቢያ ማቋቋም የሚፈልጉ አመልካቾች፤ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ የፕሮጀክት ሰነዳቸውን ከማመልከቻ ቅጽ ጋር በማያያዝ ለባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አስታውቋል። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ኢድሪስ መስሪያ ቤታቸው ለአምስቱ አዲስ የኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያዎች ባወጣው ጨረታ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ለፕሮጀክት ጥናት ሰነድ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የኤፍ ኤም የሬድዮ ሞገዶችን ፈቃድ ለመስጠት ከሚጠቀምባቸው መስፈርቶች ውስጥ፤ አመልካቾች በኘሮጀክት ጥናት ሰነዳቸው የዘረዘሯቸው የፕሮግራሞች መርሐ ግብር፣ በፕሮግራሞቹ የተካተቱ ማህበራዊ ፍላጎቶች እና ለአገልግሎቱ የተመደበው ጊዜ እንደሚገኝበት በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ላይ ተቀምጧል።

የኤፍ ኤም ሬድዮ ፈቃድ ለማግኘት በመመዘኛ መስፈርት ጥቅም ላይ ከሚውሉት ውስጥ አመልካቾች በሚያቀርቧቸው ሰነዶች ውስጥ የሚዘረዘሯቸው መሳሪያዎችና ቴክኖሎጂዎች ግምገማ አንዱ ነው

አመልካቾች በሚያቀርቧቸው ሰነዶች ውስጥ የዘረዘሯቸው መሳሪያዎችና ቴክኖሎጂዎች ከብሮድካስት አገልግሎት ቴክኖሎጂ እድገቶች ጋር አብሮ የሚሄድና የሚጠበቀውን የቴክኒክ ጥራት የሚያረጋግጥ መሆኑ ሌላኛው መስፈርት ነው። አመልካቾች አገልግሎቱን ለመስጠት ያላቸው ብቃት፣ የፋይናንስ አቅምና ምንጭ፣ አስተማማኝነት እንዲሁም ስራውን ለማስኬድ ያላቸው ዝግጁነትም በመመዘኛ መስፈርትነት ያገለግላሉ። አመልካቾች አገልግሎቱን ለመስጠት ያላቸው ተስማሚነት፣ ድርጅታዊ ብቃት፣ የሥራ ልምድና ሙያዊ እውቀትም እንዲሁ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የሬድዮ ፈቃዱን ለመስጠት በመስፈርትነት ከሚጠቀምባቸው ዝርዝር ውስጥ ተካትተዋል።  

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ እና አካባቢ የስርጭት ፍቃድ የተሰጣቸው 14 የኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያዎች ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ ሶስቱ ስርጭት ያልጀመሩ ሲሆን አንደኛው የሙከራ ስርጭት በማስተላለፍ ላይ ያለ ነው። ባጋጠሟቸው የተለያዩ ችግሮች ምክንያት እስካሁን ስርጭት ያልጀመሩት “ሐበሻ ኤፍ ኤም”፣ “ትርታ ሬዲዮ” እና “ዋርካ ሬዲዮ” የተሰኙ የኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያዎች እስከ ቀጣዩ ወር ሐምሌ መጨረሻ ድረስ ስርጭት እንዲጀምሩ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ባለፈው መጋቢት ወር የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)