ኢዜማ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን በድጋሚ መሪ አድርጎ መረጠ

በሃሚድ አወል

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲን ለመጪዎቹ ሶስት ዓመታት እንዲመሩ በድጋሚ ተመረጡ። በእርሳቸው የአመራር ስብስብ ስር ሆነው ለውድድር የቀረቡት አቶ ዮሐንስ መኮንን የፓርቲው ምክትል መሪ ሆነዋል።

የፓርቲው አመራሮች የተመረጡት ዛሬ እሁድ ሰኔ 26፤ 2014 በተካሄደው የኢዜማ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ ነው። ከትላንት ጀምሮ ሲካሄድ በቆየው በዚሁ የኢዜማ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ 900 ገደማ ጉባኤተኞች መሳተፋቸውን የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ትዕግስት ወርቅነህ ገልጸዋል።

የፓርቲው ጉባኤተኞች በሁለተኛ ቀን ውሏቸው፤ ኢዜማ ለመምራት በዕጩነት ለቀረቡት ለፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና አቶ አንዷለም አራጌ እንዲሁም የፓርቲውን ሌሎች ቁልፍ ቦታዎች ለመያዝ ለተወዳደሩ ግለሰቦች ድምጽ ሰጥተዋል። በውጤቱም መሰረት ፕሮፌሰር ብርሃኑ 549 ድምጽ በማግኘት የኢዜማ መሪነት ስልጣናቸውን አስጠብቀዋል።

ከኢዜማ ምስረታ አንስቶ የፓርቲውን የምክትል መሪነት ቦታ ይዘው የቆዩት አቶ አንዷለም አራጌ 326 ድምጽ አግኘተዋል። ኢዜማን ለመምራት በዕጩነት የቀረቡት ሶስት ተወዳዳሪዎች የነበሩ ሲሆን ሶስተኛው ተወዳዳሪ አቶ ጸጋው ታደለ ራሳቸውን ከውድድሩ አግልለዋል። 

ከአዲስ አበባ ውጭ ለመሪነት በመቅረብ ብቸኛው የነበሩት አቶ ጸጋው ራሳቸውን ከውድድር ያገለሉት ምክትላቸው የነበሩት አቶ አየለ ዳመነ “የፓርቲውን ውስጥ መስፈርት ባለማሟላታቸው” ምክንያት ከውድድር ውጭ በመሆናቸው ነው። አቶ ጸጋው ከእሳቸው ጋር ምክትል መሪ በመሆን የሚወዳደር ግለሰብ እንዲመርጡ በፓርቲው የአንድ ሳምንት ጊዜ ቢሰጣቸውም ማቅረብ አልቻሉም። 

ለፓርቲው መሪነት ተወዳድረው በተሸነፉት አቶ አንዷለም አራጌ ምትክ፤ አቶ ዮሐንስ መኮንን የኢዜማ ምክትል መሪ እንዲሆኑ ዛሬ በጉባኤተኛው ተመርጠዋል። አቶ ዮሐንስ ለተረከቡት ቦታ በሌላኛው ጎራ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት አቶ ሐብታሙ ኪታባ ነበሩ። 

ፓርቲው ከመሪ እና ምክትል መሪ ባለፈ፤ ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር፣ ጸሐፊ እና የፋይናንስ ኃላፊ ምርጫዎችንም አድርጓል። ኢዜማን በሊቀመንበርነት ለመምራት አምስት ጣምራ ዕጩዎች ለውድድር ቀርበው ነበር። ከዕጩዎቹ መካከል የአሁኑ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ እና ምክትላቸው ዶ/ር ጫኔ ከበደ ይገኙበታል።

ዶ/ር ጫኔ 435 ድምጽ በማግኘት የፓርቲውን ሊቀመንበር ሆነው ሲመረጡ፤ አቶ የሺዋስ 238 ድምጽ በማግኘት ሁለተኛ ሆነዋል። የኢዜማ የጸሐፊነት ቦታቸውን ለማስጠበቅ የተወዳደሩት አቶ አበበ አካሉ 740 የጉባኤተኞች ድምጽ በማግኘታቸው በያዙት ኃላፊነት እንደሚቀጥሉ ተረጋግጧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)