ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በ100 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቅ በፍርድ ቤት ብይን ተሰጠ

የ“ፍትሕ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ የ100 ሺህ ብር ዋስትና በማስያዝ ጉዳዩን በውጭ ሆኖ እንዲከታተል የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ብይን ሰጠ። የከፍተኛው ፍርድ ቤቱ ብይኑን በአብላጫ ድምጽ ያስተላለፈው በዐቃቤ ህግ በኩል የቀረበውን መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ ነው። ተከሳሽ በቀረበበት ክስ ላይ የሚያቀርበውን የክስ መቃወሚያ ለመስማትም ፍርድ ቤቱ ለሐምሌ 11 ቀጠሮ ሰጥቷል። 

የጋዜጠኛ ተመስገንን የወንጀል ክስ በመመልከት ላይ የሚገኘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የሕገ መንግስትና የሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ለዛሬ ሰኞ ሰኔ 27፤ 2014 ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፤ ተከሳሽ በጠበቃው አማካኝነት ያቀረበውን የዋስትና ጥያቄ መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ነበር። የተመስገን ጠበቃ የሆኑት አቶ ሄኖክ አክሊሉ የዋስትና ጥያቄውን ያቀረቡት ባለፈው ረቡዕ ሰኔ 22 ባዋለው ችሎት ነበር።

ጠበቃ ሄኖክ በወቅቱ ባቀረቡት ማመልከቻ፤ ደንበኛቸው የተከሰሱባቸው ሶስት የወንጀል አይነቶች የዋስትና መብት የማያስከለክሉ በመሆናቸው በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጥያቄ አቅርበው ነበር። የፌደራል ዐቃቤ ህግ በጋዜጠኛ ተመስገን ላይ ያቀረባቸው ሶስት ክሶች፤ “ወታደራዊ ሚስጥሮችን ላልተፈቀደለት ሰው ወይም ለህዝብ ገልጿል”፣ “የሀሰት ወይም የሚያደናግር መረጃ አሰራጭቷል”፣ “መገፋፋት እና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር ወንጀሎችን ፈጽሟል” የሚል ነው።

እነዚህ ክሶች በይፋ በችሎት በተነበቡት ባለፈው ረቡዕ፤ የጋዜጠኛው ጠበቃ የደንበኛቸው የዋስትና መብት ሊጠበቅ የሚገባባቸውን ሌሎችንም ምክንያቶች አቅርበዋል። ከምክንያቶቹ መካከል ጋዜጠኛ ተመስገን ከዚህ ቀደም በተከሰሰበት ወንጀል የተሰጠውን ዋስትና አክብሮ ፍርድ ቤት የሚቀርብ መሆኑ ነው። ጋዜጠኛው በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ኃይሎች ሀገሩን ጥሎ እንዲሰደድ በተደጋጋሚ ግፊት ቢደረግበትም በ“ሀገሬ እሞታለሁ” ብሎ እዚሁ የሚኖር መሆኑንም ጠበቃው በተጨማሪ መከራከሪያነት አቅርበው ነበር።

የፌደራል ዐቃቤ ህግ በበኩሉ “ለተከሳሹ ዋስትና ሊፈቅድለት አይገባም” ሲል የመቃወሚያ ነጥቦቹን ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በነበረው ችሎት ዘርዝሯል። ዐቃቤ ህግ ካነሳቸው መከራከሪያ ነጥቦች ውስጥ ተመስገን የፈጸማቸው ወንጀሎች “ከባድ ቅጣት የሚያስከትሉ ናቸው” የሚለው አንዱ ነው። ይህንን የዐቃቤ ህግ መከራከሪያ የመረመረው ፍርድ ቤቱ፤ በተከሳሽ ላይ ከቀረቡበት ሶስት ክሶች ውስጥ ከባድ የሆነው አንደኛው ብቻ መሆኑን ገልጿል። ዐቃቤ ህግ ስለ ቀሪዎቹ ተያያዥ ሁለት ክሶች ያቀረበው ማብራሪያ፤ ፍርድ ቤቱ “ከባድ ወንጀል ናቸው” የሚለውን ግንዛቤ ሊወስድ እንዳላስቻለውም በዛሬው ብይን ተጠቅሷል። 

ዐቃቤ ህግ ለፍርድ ቤት ያቀረበው ሌላው መቃወሚያ፤ ተከሳሹ የዋስትና መብቱ ቢጠበቅለት “ግዴታውን አክብሮ ፍርድ ቤት አይቀርብም” የሚል ነው። ይህንንም የዐቃቤ ህግ መከራከሪያ ፍርድ ቤቱ አለመቀበሉን በዛሬው ብይኑ አስታውቋል። ተከሳሹ በዋስትና ቢወጣ “የተጠረጠረበትን ወንጀል በድጋሚ ሊፈጽም ይችላል” በሚል በከሳሽ በኩል የቀረበውን መከራከሪያም ፍርድ ቤቱ በተመሳሳይ ሁኔታ ሳይቀበለው ቀርቷል።

በፕሬስ ላይ የሚደረግ ቅድመ ምርመራ በህግ መከልከሉን የጠቀሰው ፍርድ ቤቱ፤ ተከሳሽ በጋዜጠኝነቱ ወንጀል ሊፈጽም ይችላል በማለት አስቀድሞ ከመጻፍ እንዲታቀብ ማድረግ “በእጁ አዙር የቅድመ ምርመራን” መፍቀድ መሆኑን አስገንዝቧል። በመጽሔት ላይ የሚታተሙ ጽሁፎችን የመወሰን ስልጣን ያለው የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ መሆኑን በመጥቀስም፤ ተከሳሹ ከመጻፍ ሊታገድ እንደማይገባ አብራርቷል። 

ተመስገን ቋሚ አድራሻ ያለው መሆኑን በስተመጨረሻ የጠቀሰው ፍርድ ቤቱ፤ የተከሳሽ የዋስትና መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል በማለት በአብላጫ ድምጽ ብይን መስጠቱን አስታውቋል። የተከሳሽን ጉዳይ ከሚመለከቱ ሶስት ዳኞች ውስጥ የቀኝ ዳኛው በብይኑ ላይ የልዩነት ሃሳብ እንዳላቸው በመግለጽ ይህንኑ አስምተዋል። 

በወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው የዋስትና መብቱ ሊከበርለት እንደሚገባ በህገመንግስቱ የተገለጸ ቢሆንም፤ ይህ መብት “በልዩ ሁኔታ ሊገድብ እንደሚችል” በራሱ በህገ መንግስቱ መገለጹን ዳኛው በማብራሪያቸው ላይ አንስተዋል። ተከሳሹ የተጠረጠረበት ወንጀል የዋስትና መብት ሊያስከለክል ይችላል ወይ? የሚለው በፍርድ ቤት መመዘን ያለበት ከቀረቡበት ክሶች “ብዛት” እና ከጉዳዩ “ክብደት” አንጻር እንደሆነም ገልጸዋል። 

በተከሳሹ ላይ ሶስት ተደራራቢ ክሶች መቅረባቸውን የጠቆሙት ዳኛው፤ “ተከሳሹ ተላልፈዋል የተባሉት የወንጀል ድንጋጌዎች ከባድነት ያላቸው መሆኑን ከቀረበው ክስ መረዳት ይቻላል” ብለዋል። ተከሳሹ ከ2011 ጀምሮ በ“ፍትሕ” መጽሔት ላይ በወንጀል  የተጠረጠሩባቸውን ጹሁፎች በተደጋጋሚ አትመው የሚያሰራጩ እንደነበሩ የጠቀሱት ዳኛው፤ በዋስትና ቢወጡ በ“ፍትሕ” መጽሔት ላይ መጻፍ እንደሚቀጥሉ በቀደመው ችሎት በጠበቃቸው በኩል መገለጹን አስታውሰዋል። 

ተከሳሹ የዋስትና መብታቸው ቢጠበቅላቸው “ግዴታቸውን የማይፈጽሙ”፣ “ሌላ ወንጀል የመፈጽም ዕድል ያላቸው በመሆኑ” እና “የተከሰሱበት ወንጀል ልዩ ባህሪ ያለው ስለሆነ” የዋስትና መብት ሊፈቅድላቸው አይገባም በሚል ከስራ ባልደረቦቻቸው የተለየ የውሳኔ ሃሳብ እንዳላቸው ዳኛው አብራርተዋል። ፍርድ ቤቱ የልዩነት ሃሳቡን ካደመጠ በኋላ፤ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የ100 ሺህ ብር ዋስትና በማስያዝ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነ እንዲከራከሩ ትዕዛዝ ሰጥቷል። 

ፍርድ ቤቱ ለጋዜጠኛ ተመስገን የዋስትና መብቱን ቢያስጠብቅለትም፤ በተከሳሹ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ጥሏል። በዚህ ውሳኔ መሰረትም ተከሳሹ ከሀገር እንዳይወጣ ለኢሜግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤት ደብዳቤ እንዲጻፍ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ በተከሳሹ በኩል የሚቀርበውን የክስ መቃወሚያ ለመስማትም ለዛሬ ሁለት ሳምንት ሐምሌ 11፤ 2014 ቀጠሮ በመስጠት የዛሬውን የችሎት ውሎ አጠናቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)