በሃሚድ አወል
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በኦሮሚያ ክልል ስር ያሉት ሶስት የወለጋ ዞኖች “ላልተወሰነ ጊዜ” ከፌዴራሉ መንግስት በሚመደቡ የሲቪል እና የጸጥታ አስተዳደር አካላት እንዲተዳደሩ ጠየቀ። አብን በፌደራል መንግስቱ ስር እንዲተዳደሩ የጠየቀው የምዕራብ፣ ምስራቅ እና ቄለም ወለጋ ዞኖችን ነው።
ተቃዋሚ ፓርቲው ይህን ጥያቄ ያቀረበው ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 28፤ 2014 ከሰዓት ባወጣው መግለጫ ነው። ሶስቱ የወለጋ ዞኖች “በተደጋጋሚ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈጸመባቸው ነው” ሲል የወነጀለው አብን፤ “አካባቢዎቹን የማስተዳደር ስልጣን ላልተወሰነ ጊዜ ሙሉ በሙሉ በፌዴራል መንግስት ስር እንዲውል እንዲያደርግ” የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ጠይቋል።
ሀገር አቀፉ ፓርቲ ይህን መግለጫ ያወጣው፤ በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን በርካታ ነዋሪዎች በታጣቂዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው። በነዋሪዎቹ ላይ የተፈጸመውን ግድያ በመጀመሪያ ይፋ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትላንት ሰኞ ምሽት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ “በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ጭፍጨፋ ተፈጽሞባቸዋል” ብለዋል። በዜጎች ላይ እየደረሰ ነው ባሉት “መከራ” ማዘናቸው የገለጹት አብይ፤ ለጥቃቱ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተሰየመውን “የሸኔ ቡድን” ተጠያቂ አድርገዋል።
ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም (ኢሰመኮ) ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫ፤ የቄለም ወለጋውን ጥቃት የፈጸሙት “ሸኔ” በሚል መጠሪያ የሚታወቁት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላት መሆናቸውን ከምንጮቹ መረዳቱን አስታውቋል። ትላንት ሰኞ ሰኔ 27፤ 2014 ጠዋት ላይ በተፈጸመው በዚህ ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መገደላቸውንም ገልጿል።
የትላንቱ ጥቃት ዋነኛ ኢላማ የነበሩት በቄለም ወለጋ ዞን በሀዋ ገላን ወረዳ መንደር 20 እና 21 በተባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች መሆናቸውን ኮሚሽኑ በመግለጫው አመልክቷል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በአካባቢው የቀጠለው የጸጥታ ችግርና በነዋሪዎች ላይ እየደረሰ ያለው ብሔር ተኮር ግድያ በአስቸኳይ መቆም አለበት” ሲሉ አሳስበዋል።
በሁለቱ የቄለም ወለጋ መንደሮች የተፈጸመውን ጥቃት “ጭፍጨፋ” ሲል የጠራው ኢሰመኮ፤ ተጨማሪ የንጹሃንን ሞት ለመከላከል መንግስት የጸጥታ ኃይሉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርቧል። በቄለም ወለጋ የተፈጸመው “የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው” ሲል የከሰሰው አብን በበኩሉ፤ ጥቃቱን ያወገዙት የመንግስት ባለስልጣናት እና የተወካዮች ምክር ቤት “ወንጀሉን በስሙ እንዲጠሩት” ጠይቋል።
የመንግስት ባለስልጣናት “ወንጀሉን ከማውገዝ ባለፈ ተጨባጭ እርምጃዎች” እንዲወስዱ ፓርቲው በዛሬው መግለጫ ጥሪውን አስተላልፏል። አብን ሊወሰዱ ይገባቸዋል በሚል በመግለጫው ከጠቀሳቸው እርምጃዎች ውስጥ “በምዕራብ፣ ምስራቅ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች ያሉ የሲቪል እና የፖሊስ አስተዳደር አባላት በህግ መጠየቅ የሚለው” ይገኝበታል።
የፌደራሉ መንግስት እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “በዘር ማጥፋት እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መከላከል የሚያስችል ብሔራዊ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ ሕግ እና አሰራር ስራ ላይ” እንዲያውሉ የሚጠይቀው ሌላው በፓርቲው መግለጫ የተጠቀሰ እርምጃ ነው። በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ነው ያለውን “የዘር ፍጅት” “ግዙፍ የብሔራዊ ስጋት” መሆኑን የጠቀሰው ተቃዋሚ ፓርቲው፤ መንግስት እና ፓርላማው ይህንን ወንጀል መከላከል ይገባቸዋል ብሏል።
የፌደራል እና የክልል መንግስታት “ለጥቃት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች በቂ የስጋት ትንተና እንዲሰሩ እና ቀጣይ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችል በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ” አብን በአጽንኦት ጠይቋል፡፡ መንግስት ለጥቃት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን በማደራጀት እንዲያስታጥቃቸው እና ራሳቸውን የመከላከል የሚችሉበትን ሁኔታ እንዲፈጥርም ሀገር አቀፍ ፓርቲው ጥሪውን አቅርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)