የተወካዮች ምክር ቤት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በልዩ ስብሰባ እየመከረ ነው

በሃሚድ አወል

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “በወቅታዊ የሀገሪቱ የጸጥታ ጉዳይ እና በንጹሃን ዜጎች ጭፍጨፋ” ላይ ለመወያየት ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 29፤ 2014 ልዩ ስብሰባ እያካሄደ ነው። ፓርላማው በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ “የውሳኔ ሃሳብ” ያሳልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አንድ የፓርላማ አባል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

የተወካዮች ምክር ቤት ቀደም ሲል ለዛሬ ይዞት የነበረው መርሃ ግብር በፓርላማ አባላት አማካኝነት የችግኝ ተከላ ማካሄድ ነበር። ነገር ግን ከአማራ ክልል የተወከሉ የምክር ቤት አባላት ኮሚቴ አዋቅረው ባቀረቡት ጥያቄ የዛሬው ልዩ ስብሰባ መጠራቱን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የፓርላማ ምንጭ ተናግረዋል። 

በኮሚቴው ውስጥ ከአማራ ክልል የተወከሉ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ እንዲሁም የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዮች መካተታቸውን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የፓርላማ አባል አስረድተዋል። በኮሚቴው ጥያቄ በተጠራው በዛሬው ስብሰባ የተወካዮች ምክር ቤት “ጭፍጨፋውን ያወግዛል ተብሎ እንደሚጠበቅ” እኚሁ የፓርላማ አባል ገልጸዋል።

ከትላንት በስቲያ ሰኞ ሰኔ 27 በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን ውስጥ የሚገኙ ዜጎች “ጭፍጨፋ” እንደተፈጸመባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስታውቀው ነበር። በቄለም ወለጋ ዞን በሀዋ ገላን ወረዳ መንደር 20 እና 21 በተባሉ አካባቢዎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም አረጋግጧል። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኞ ምሽት ባወጣው መግለጫ “በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን ውስጥ የሚገኙ ንጹሀን ዜጎቻችን ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ በእጅጉ የሚወገዝ ነው” ብሎ ነበር። ምክር ቤቱ በዛሬው ልዩ ስብሰባው ድርጊቱን በይፋ ከማውገዝ ባለፈ “ጉዳዩን ገምግሞ ሪፖርት የሚያቀርብ ቡድን” ሊያወቅር እንደሚችልም የፓርላማ አባሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል። ምክር ቤቱ ሊያሳልፈው በሚችለው የውሳኔ ሀሳብ መሰረትም “ብሔራዊ የሀዘን ቀን ሊታወጅ” የሚችልበት ዕድል እንዳለም ጠቁመዋል። 

በዚህ ጉዳይ ላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። የዛሬውን የፓርላማ ልዩ ስብሰባን የመዘገብ ፍቃድ የተሰጠው ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ብቻ በመሆኑም ሂደቱን በተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ ተገኘቶ ለመከታተልም አልተቻለም። 

የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢን ጨምሮ ዛሬ በፓርላማ ሊካሄድ የነበረን ሌላ ስብሰባ ለመዘገብ በስፍራው የተገኙ የግል መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች “መግባት አትችሉም” ተብለው ተመልሰዋል። የግል መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በፓርላማው የተገኙት፤ በተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት የሚገመግምበትን ስብሰባ ለመዘገብ ነበር። 

ይህ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ በልዩ ውይይቱ ምክንያት መሰረዙን የፓርላማ ምንጮች አስረድተዋል። የተወካዮች ምክር ቤት ትላንት ማክሰኞ ሰኔ 28፤ 2014 ሊካሄደው የነበረው 16ኛ መደበኛ ስብሰባ እንዲሁ ሳይካሄድ ቀርቷል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የፓርላማ አባላት፤ የትላንቱ መደበኛ ስብሰባ የተሰረዘበት ምክንያት አልተገለጽልንም ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)