ፓርላማው ከሰሞኑ የተፈጸሙ ግድያዎችን የሚያጣራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ወሰነ

በሃሚድ አወል

ከሰሞኑ በኦሮሚያ እና ጋምቤላ ክልሎች የተፈጸሙ ግድያዎችን ጨምሮ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች ላይ የተፈጸሙ ኢ-ሰብዓዊ ጭፈጨፋዎችን የሚያጣራ ልዩ ኮሚቴ እንዲቋቋም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወሰነ። በፓርላማው የበላይ አመራር የሚሰየመው ይህ ልዩ ኮሚቴ “ለቀጣይ እርምጃዎች የሚረዳ ምክረ ሃሳብ” እንዲያቀርብ ኃላፊነት ተጥሎበታል። 

የተወካዮች ምክር ቤት ይህን ውሳኔ ያሳለፈው ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 29፤ 2014 ባካሄደው 6ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ ነው። በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ እና የዜጎችን ጸጥታ እና ደህንነት ለማስጠበቅ በተንቀሳቀሱ የጸጥታ አካላት ላይ የደረሰውን የህይወት መጥፋት “እጅግ የሚኮነን” መሆኑን ፓርላማው አስታውቋል። በዚህ መሰረት ካካሄደው ውይይት በኋላም ስድስት ውሳኔዎችን አሳልፏል። 

ከውሳኔዎቹ ዝርዝር በቀዳሚነት የተቀመጠው “በግፍ ለተጨፈጨፉ ዜጎች የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት እንዲደረግ” የሚለው ነው። ይህን ተከትሎም በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ የተሳተፉ የፓርላማ አባላት የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት አድርገዋል። 

ብሔራዊ የሀዘን ቀን እንዲታወጅ በዛሬው ልዩ ስብሰባ ጥያቄ ቢቀርብም፤ ምክር ቤቱ ለጊዜው ይህን አካሄድ ሳይከተል ቀርቷል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “መጀመሪያ በህገ መንግስቱ መሰረት ሂደቱን ጠብቆ መታወጅ ካለበት ህጉን እንመልከት እና ምንም ችግር የለውም። እዚሁ አምጥተን ጸድቆ ይታወጃል” ማለታቸውን በዛሬው ስብሰባ ላይ የተሳተፉ አንድ የፓርላማ አባል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።   

የተወካዮች ምክር ቤት በሁለተኛነት እና በሶስተኛነት ያሳለፈው ውሳኔ ተጠያቂነትን የሚመለከት ነው። “በአገራችን በየትኛውም ክልልና አካባቢ በሲቪል ዜጎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት ያስከተሉ እና ንብረት ያወደሙ ግለሰቦች በሕግ እንዲጠየቁ እንዲደረግ” ሲል ምክር ቤቱ በውሳኔው ላይ አስፍሯል። 

“በየደረጃው ያለው አመራር፣ የጸጥታ አካል እና የፍትህ ተቋም” አጥፊዎችን ለሕግ ተጠያቂነት እንዲያቀርቡ እንዲያደርጉ ምክር ቤቱ ወስኗል። እነዚህ አካላት የህዝቡን ደህንነት እና ሰላም በጥብቅ እንዲያስከብሩ ፓርላማው ውሳኔ አስተላልፏል። በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በደረሱ ጥቃቶች “ከመንደራቸው እና ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ስራ በአስቸኳይ እንዲሰራም” ምክር ቤቱ በውሳኔው አስቀምጧል። 

ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ “አስቸጋሪ ጊዜ” ሲል የጠራው የፓርላማው ውሳኔ፤ በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝቦች ከየትኛውም ግዜ በላይ በወንድማማችነት እና በአንድነት እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል። ባለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ “አስከፊ እና ከፋፋይ የዘር ጥላቻ ተዘርቷል” ሲል የወነጀለው ፓርላማው፤ ይህም “በህዝብ ውስጥ ዘግናኝ እና አስከፊ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ በር ከፍቷል” ብሏል። 

ከዚህም የተነሳ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች “ኢ-ሰብአዊ ጭፍጨፋ በዜጎች ላይ ሊፈጸም ችሏል” ያለው የተወካዮች ምክር ቤት፤ እነዚህን ድርጊቶች የሚያጣራ “ልዩ ኮሚቴ” እንዲቋቋም ወስኗል። በምክር ቤቱ “የበላይ አመራር ይሰየማል” የተባለው የእዚህ ኮሚቴ አባላት ስብጥር “ሁሉንም ብዝሃነቶች ታሳቢ ያደረገ” እንደሚሆን ተገልጿል።

የኮሚቴው አባላት ማንነትን በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው በዛሬው ልዩ ስብሰባ ላይ የተሳተፉ አንድ የፓርላማ አባል፤ “ልዩ ኮሚቴው እንዲቋቋም ውሳኔ ከመተላለፉ በስተቀር ምንም የተነገረ ነገር የለም፤ ገና ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ኮሚቴው የሚቋቋምበትን ሂደት በተመለከተ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ “በቋሚ ኮሚቴም በአስተባባሪ ኮሚቴም ተመልክተን፤ ሁሉንም በሚያካትት መልኩ ብዝሃነትን ጠብቀን እናቋቁማለን። ከዛ እናቀርብላችኋለን” ማለታቸውን እኚሁ የፓርላማ አባል ገልጸዋል።

የግል መገናኛ ብዙሃን የዘገባ ፍቃድ ባላገኙበት በዛሬው ልዩ ስብሰባ ላይ 17 የሚሆኑ የምክር ቤት አባል አስተያየት መስጠታቸውን የፓርላማ አባሉ ገልጸዋል። በልዩ ስብሰባው ላይ “መንግስት ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም፤ መንግስት ኃላፊነቱን ይወጣ” እንዲሁም “የመንግስት ሹማምንት እጃቸው አለበት እና መንግስት ራሱን ያጥራ” የሚሉ ሀሳቦች ተደጋግመው መነሳታቸውን የምክር ቤት አባሉ አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)