የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ዓመታዊ ሪፖርት ነገ ይፋ ሊደረግ ነው

በተስፋለም ወልደየስ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ሁኔታን የሚዳስስ የመጀመሪያውን ዓመታዊ ሪፖርት ነገ አርብ ሐምሌ 1፤ 2014 ይፋ ሊያደርግ ነው። ኮሚሽኑ ዓመታዊ ሪፖርቱን ለተወካዮች ምክር ቤት በንባብ ለማቅረብ እቅድ ቢይዝም ፓርላማው “በአስቸኳይ ጉዳዮች” ምክንያት በመጠመዱ ምክንያት እንዳልተሳካለት ምንጮች ገልጸዋል። 

ኢሰመኮ በአዲስ መልክ ከተቋቋመ ወዲህ ሲቀርብ የመጀመሪያ የሆነው ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሪፖርት፤ ከሰኔ 2013 እስከ ሰኔ 2014 ድረስ ያለውን ጊዜ የሚሸፈን መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል። ሪፖርቱ ኢሰመኮ በልዩ ልዩ የስራ ዘርፎቹ እና ጽህፈት ቤቶቹ አማካኝነት በሰበሰባቸው መረጃዎች ላይ በመመርኮዝ በዓመቱ ውስጥ የነበረውን አጠቃላይ ሀገራዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ የሚዳስስ ነው ተብሏል።

ሪፖርቱ 10 የሰብዓዊ መብት ዘርፎችን እንደሚሸፍን የኢሰመኮ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ ጠቁመዋል። የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች አካል በሆነው በህይወት የመኖር መብት ስር፤ በሀገሪቱ ባለፈው አንድ ዓመት የተፈጸሙ ግድያዎች አጠቃላይ ዳሰሳ መደረጉን እኚሁ ምንጭ ገልጸዋል። በሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ስር የተካተተው “ከአስገድዶ መሰወር የመጠበቅ መብት” የተተገበረበት ሁኔታ በሪፖርቱ መቅረቡንም አመልክተዋል።    

ዓመታዊ ሪፖርቱ በማረሚያ ቤት፣ በፖሊስ ጣቢያ እና በኢ-መደበኛ ማቆያ ቦታዎች በጥበቃ ስር ያሉ ሰዎችን የአያያዝ ሁኔታ እንደሚዳስስ ተነግሮለታል። ኢሰመኮ በስድተኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ባደረገው የሰብዓዊ መብት ክትትል ላይ የተመረኮዘ አጠቃላይ ዕይታም በሪፖርቱ ተካትቷል። የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርቱ ለኮሚሽኑ በግል የቀረቡ አቤታቱዎች ላይ ተመስርቶ የሰጣቸው ትንታኔዎችንም ይዟል።      

ኢሰመኮ በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ሁኔታን የሚዳስስ ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያቀርብ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ከዚህ ቀደም በፓርላማ በቀረቡበት ወቅት ተናግረው ነበር። ኢሰመኮን ያቋቋመው አዋጅ፤ መስሪያ ቤቱ መደበኛ ሪፖርቶችን እንደሚያቀርብና አሰራሩን ለህዝብ ግልጽ ማድረግ እንደሚኖርበት ይደነግጋል። 

ኮሚሽኑ የ10 ወራት የስራ ክንውን ሪፖርቱን ባለፈው ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ ለተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ማቅረቡ ይታወሳል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር፤ ሀገራዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ የሚዳስስ ለዋናው ምክር ቤት እንደሚያቀርቡ በወቅቱ አስታውቀው ነበር።

ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነው ኢሰመኮ፤ ዓመታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርቱን ለማቅረብ አቅዶ የነበረው የፓርላማ አባላት ለዕረፍት ከመበተናቸው በፊት ነበር። ይህን የኮሚሽኑን ጥያቄ የተቀበለው የተወካዮች ምክር ቤት፤ ዓመታዊ ሪፖርቱ ከሁለት ሳምንት በፊት ለፓርላማ እንዲቀርብ ጊዜ አመቻችቶ እንደነበር የኢሰመኮ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ አስታውቀዋል።

ሆኖም ፓርላማው “በሌሎች አስቸኳይ ጉዳዮች በመያዙ ምክንያት ሪፖርቱ በአካል መቅረቡ ቀርቶ በጹሁፍ ለፓርላማው እንዲቀርብ ተደርጓል” ሲሉ እኚሁ የመስሪያ ቤቱ ምንጭ ገልጸዋል። በፌደራል ሕገ መንግስት መሰረት ነጻ ፌደራላዊ የመንግስት አካል ሆኖ የተቋቋመው ኢሰመኮ፤ ለሰብአዊ መብቶች መስፋፋት፣ መከበርና እና ጥበቃ የሚሰራ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)