ኢሰመኮ፤ ኢትዮጵያ አሳሳቢ የሰብዓዊ መብት ቀውስ ውስጥ መሆኗን አስታወቀ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኢትዮጵያ አሳሳቢ የሰብዓዊ መብት ቀውስ ውስጥ እንደምትገኝ አስታወቀ። ኮሚሽኑ ይህን ያስታወቀው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርቱን ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው።

ኢሰመኮ ዓመታዊ ሪፖርቱን ዛሬ አርብ ሐምሌ 1፤ 2014 ይፋ ያደረገው መስቀል አደባባይ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። በዚሁ መግለጫ ላይ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ሀገሪቷ ያለችው ምንም የማይካድ አሳሳቢ የሆነ ሰብዓዊ መብቶች ቀውስ ውስጥ ስለሆነ፤ በርካታ አሳሳቢ ጉዳዮች በየዘርፉ አሉ” ሲሉ የሀገሪቱን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ግምገማ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል። 

በኮሚሽኑ የሲቪል እና ፖለቲካዊ መብቶች ኮሚሽነሩ ዶ/ር አብዲ ጂብሪል፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶችን አሳሳቢ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ “መንግስታዊ ባልሆኑ ተዋናዮች” የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየጨመሩ መምጣታቸውንም ጠቁመዋል። 

የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት “በዋናነት መንግስታዊ ካልሆኑት ከታጣቂ ቡድኖች መምጣታቸው” ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር አስቸጋሪ እንዳደረገው ዶ/ር አብዲ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል። በዛሬው መግለጫ ላይ ይፋ በተደረገው የኢሰመኮ ሪፖርትም ይኸው እውነታ ተደጋግሞ ተስተጋብቷል። 

ለሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ቅድሚያ የሰጠው ሪፖርቱ፤ በህይወት የመኖር መብትን በዳሰሰበት ክፍል “ባለፉት 12 ወራት በህይወት የመኖር መብት እጅግ የከፋ አደጋ ውስጥ እንደወደቀ ቀጥሏል” ሲል አትቷል። ኮሚሽኑ በሪፖርቱ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በአማራ እና አፋር ክልሎች እንዲሁም በኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ሶማሌ ክልሎች የተፈጸሙ የሲቪል ሰዎች ግድያን በማሳያነት ጠቅሷል።

ኢሰመኮ በአማራ እና በአፋር ክልል ለተፈጸሙ ግድያዎች በሁሉም ወገኖች ያሉ የጦርነቱን ተሳታፊዎች ተጠያቂ ሲያደርግ፤ በኦሮሚያ ክልል ለተፈጸሙት ግድያዎች ደግሞ “ኦነግ ሸኔ” የተባለው ቡድንን ወንጅሏል። በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከጭካኔ፣ ኢ-ሰብዓዊ እና አዋራጅ አያያዝ ቅጣት ነጻ የመሆን መብቶች መጣሳቸውንም ኮሚሽኑ አስታውቋል። 

መብታቸው የተጣሰባቸው አብዛኛዎቹ ሲቪል ሰዎች መሆናቸውን እና በጦርነቱ ተሳትፈው የተማረኩ ተዋጊዎችም ለዚህ መብት ጥሰት መጋለጣቸውን አስታውቋል። ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በቆየችባቸው ከጥር እስከ የካቲት ባሉት ሶስት ወራት ገደማ “መጠነ ሰፊ የዘፈቀደ እስር፣ ብሔርን መሰረት ያደረገ አድሏዊ አሰራር፣ እስራት እና ያለ አግባብ ከስራ እና ከደመወዘ መታገድ ተፈጽሟል” ብሏል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በትግራይ ክልልም ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት መሆኑን ኢሰመኮ አስታውቋል። ከሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና ደንብ በማውጣት የትግራይ ክልልን እያስተዳደረ መሆኑን ያስታወቀው ኮሚሽኑ፤ ህወሓት ያወጣው አዋጅ “የሰዎችን መብቶች በከፍተኛ ሁኔታ የገደበ እና ከኢትዮጵያ ህገ መንግስት እና የወንጀል ህግ ጋር የሚጣረስ ነው” ሲል ነቅፎታል።

አዋጁ ከፌደራል መንግስት ጋር የሚደረግ የስራ ግንኙነት በወንጀል የሚያስጠይቅ እና ወላጆች በግዳጅ ልጆቻቸው የህወሓትን ሰራዊት እንዲቀላቀሉ የሚያስገድ መሆኑን ኢሰመኮ ገልጿል። በአስር ዘርፎች ተከፋፍሎ የቀረበው ዓመታዊ ሪፖርቱ፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በነበሩ ግጭቶች የሴቶች እና ህጻናት መብቶች መጣሳቸውንም አመልክቷል።  

በግጭቶቹ “በርካታ ሴቶች እና ህጻናት ላይ መጠነ ሰፊና ስልታዊ በሆነ መንገድ በተናጠል እና በቡድን የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች መፈጸማቸውን” ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል። ጥቃቶቹ “ሰብዓዊ ክብርን ለማዋረድ ሆነ ተብሎ ታቅዶ በግልጽ የበቀል ስሜት የተፈጸሙ” መሆናቸውን የገለጸው የኮሚሽኑ ሪፖርት፤ ጥቃቶቹ በጦርነት አውድ ውስጥ በመፈጸማቸው የጦር ወንጀል ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁሟል። 

በመቶ ገጾች የተዘጋጀው ዓመታዊው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርቱ፤ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ላይ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንም ዳስሷል። ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል ካለፈው ዓመት ሐምሌ እስከ ግንቦት 2014 ባሉት ጊዜያት፤ 54 የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ከቀናት እስከ በርካታ ወራት በእስር ላይ መቆየታቸው በሪፖርቱ ተገልጿል። ከእነዚህ መገናኛ ብዙሃን መካከል 15ቱ በትግራይ ባለስልጣናት በክልሉ የተያዙ መሆናቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

በትግራይ ክልል የታሰሩ የመገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ በክልሉ ስላለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ኮሚሽኑ መረጃ ስላገኘበት መንገድ፤ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጥያቄ ተነስቶ ነበር። ጥያቄው የቀረበላቸው የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል፤ እስከ ቅርብ ጊዜያት ድረስ መቀሌ የሚገኘው የኮሚሽኑ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ ላይ እንደነበር ገልጸዋል። 

ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም “ከተወሰኑ ወራቶች በፊት የትግራይ ባለስልጣናት መቀሌ ላይ ያለውን ጽህፈት ቤታችንን ዘግተውብናል። ያ ቢሮ ስለተዘጋ ከዚህ በፊት የነበረንን አይነት ክትትል ለማድረግ እንቅፋት ፈጥሮብናል” ብለዋል። ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ አሁንም የርቀት ክትትል በማድረግ መረጃዎችን እንደሚያገኝ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)