በሃሚድ አወል
ላለፉት ሁለት ዓመታት በኮሮና በሽታ የተያዙ ህሙማን ሲታከሙበት የቆየው የሚሊኒየም አዳራሽ በቅርቡ ወደ መደበኛ ስራው ሊመለስ ነው። በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘውን ይህን አዳራሽ ወደ ኮቪድ-19 ህክምና ማዕከልነት ቀይሮ ሲጠቀምበት የነበረው የጤና ሚኒስቴር፤ በመጪው ቅዳሜ በባለቤትነት ለሚያስተዳድረው ድርጅት በይፋ እንደሚያስረክብ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቋል።
ንብረትነቱ የባለሐብቱ ሼህ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲን በሆነው አዲስ ፓርክ ዲቨሎፕመንት እና ማኔጅመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስር የሚተዳደረው ሚሊኒየም አዳራሽ ወደ ኮቪድ 19 ማከሚያነት የተቀየረው ከሁለት ዓመት በፊት ሚያዚያ አጋማሽ 2012 ዓ.ም ነበር። ከግንቦት 2012 ጀምሮ የኮሮና ህሙማንን ሲያስተናግድ የቆየው አዳራሹ እስካለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።
በአዳራሹ ሲታከሙ የነበሩ እና ያገገሙ የመጨረሻዎቹ የኮቪድ 19 ህሙማን የህክምና ማዕከሉን ሙሉ ለሙሉ ለቅቀው የወጡት ከ10 ቀናት ገደማ በፊት መሆኑን በጤና ሚኒስቴር ብሔራዊ የኮቪድ 19 ምላሽ ግብረ ኃይል አስተባባሪ ዶ/ር መብራቱ ማሴቦ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የጤና ሚኒስቴር የሚሊኒየም አዳራሽን በባለቤትነት ለሚያስተዳድረው ድርጅት ለመመለስ የወሰነው በኮሮና በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ እና ህክምናው የሚሰጡ ሌሎች ተቋማት ቁጥር በመጨመሩ መሆኑን ዶ/ር መብራቱ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የኮሮና በሽታ አሁንም በወረረሽኝ ደረጃ ያለ ቢሆንም የቫይረሱ ስርጭት ግን ዝቅተኛ መሆኑን የግብረ ኃይሉ አስተባባሪ አስረድተዋል። እንደ ዶ/ር መብራቱ ገለጻ፤ ለኮሮና ቫይረስ ስርጭት መቀነስ አንደኛው ምክንያት በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ክትባትን የተከተቡ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆን ነው። በጤና ሚኒስቴር መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ 42.8 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ክትባት ተከትበዋል።
ዶ/ር መብራቱ “ብዙ ሰው ስለተከተበ አሁን ሆስፒታል ገብቶ የሚታከመው እንደ ድሮው ያን ያህል ብዙ አይደለም” ሲሉ ክትባቱ ያመጣውን ለውጥ ያብራራሉ። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 16,037 ሰዎች የኮቪድ-19 ቫይረስ እንዳለባቸው በምርመራ መረጋገጡን የጤና ሚኒስቴር ዕለታዊ መረጃ ያመልክታል። ሚኒስቴሩ ትላንት ሰኞ ሐምሌ 4፤ 2014 ባወጣው በዚሁ መረጃ መሰረት፤ 53 ታማሚዎች በጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ሆነው ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛል።
የጤና ሚኒስቴር እስካሁን ካከናወናቸው አምስት ሚሊዮን ገደማ የላብራቶሪ ምርምራዎች ውስጥ የኮቪድ-19 ቫይረስ የተገኘባቸው 490, 895 ሰዎች ናቸው። ከእነዚህ የኮሮና ህሙማን መካከል 466 ሺህ ያህሉ ሲያገግሙ 7,552 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ህይወታቸውን አጥተዋል።
የኮሮና በሽታ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ መገኘቱ ከተረጋገጠበት ከመጋቢት 2012 ጀምሮ ለመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት በብቸኝነት ህሙማንን ሲያስተናግድ የቆየው የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ነበር። የአእምሮ ህክምናን በዋነኛነት ለመስጠት የተቋቋመው ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል፤ የኮሮና በሽታ ህሙማንን ሲያስተናግድ የቆየው ባሉት 600 መቶ ገደማ አልጋዎች ነበር።
የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያ እየተስፋፋ በመጣበት ወቅት፤ የጤና ሚኒስቴር የሚሊኒየም አዳራሽን ጨምሮ ለለይቶ ማከሚያ የሚያገለግሉ ህንጻዎችን እና ቦታዎችን ከበጎ ፍቃደኛ ግለሰቦች በጊዜያዊነት ተረክቦ የህክምና አገልግሎቱን በእነዚህ ቦታዎች ሲሰጥ ቆይቷል። የንግድ ትርዒት እና ባዛሮችን እንዲሁም የሙዚቃ ኮንሰርቶችን በማስተናገድ የሚታወቀው የሚሊኒየም አዳራሽ የህክምና ማዕከልነት ስራውን የጀመረው በ1,040 የህሙማን አልጋዎች ነው።
ካሉት አልጋዎች ውስጥ 40 ያህሉን ለጽኑ ህሙማን መድቦ የነበረው የሚሊኒየም አዳራሽ የህክምና ማዕከል፤ የኮሮና ወረርሽኝ በበረታበት ወቅት ህሙማንን የማስተናገድ አቅሙ በእጅጉ ተፈትኖ እንደነበር ዶ/ር መብራቱ ያስታውሳሉ። ኢትዮጵያ በአራት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ማዕበሎች ማለፏን የሚያነሱት የህክምና ባለሙያው ከጥር 2013 እስከ ሚያዚያ 2013 ያሉት ወራት “ስርጭቱ በጣም ከፍተኛ ሆኖ ችግር ውስጥ የገባንበት ጊዜ ነበር” ይላሉ።
ይህ ጊዜ “የኦክስጅንም፤ የአልጋም ዕጥረት ከፍተኛ የነበረበት ነው” የሚሉት የብሔራዊ የኮቪድ 19 ምላሽ ግብረ ኃይል አስተባባሪ፤ “አልጋ ጠፍቶ ቤት የሚጠብቅ የኮቪድ ታማሚ ነበረን” ሲሉ በወቅቱ የነበረውን የወረርሽኙን አስቸጋሪነት ይገልጻሉ። የሚሊኒየም አዳራሹ የኮሮና ህክምና ማዕከል የጽኑ ህሙማን ማከሚያ አልጋዎቹን በጊዜው ወደ 100 ለማሳደግ ተገድዶ እንደነበርም ያስረዳሉ።
በኢትዮጵያ ያለው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ የጤና ሚኒስቴር በጊዜያዊነት የተረከባቸውን አብዛኞቹን ማቆያዎች ከዓመት በፊት መልሷል። ሚኒስቴሩ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሲገለገልበት የቆየውን የሚሊኒየም አዳራሽንም ቢሆን የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በሚገኙበት ይፋዊ ስነ ስርዓት በመጪው ቅዳሜ ለባለቤቶቹ እንደሚመልስ ዶ/ር መብራቱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
“አሁን 637 ተቋማት ኮቪድን ማከም ጀምረዋል። እዚያው በተቋማቸው በተለየ ቦታ ማለት ነው። [ስለዚህ] እንደ ድሮው ለብቻ ለይቶ የሚያክም ተቋም አያስፈልገንም” ሲሉ የሚሊኒየም አዳራሽ ወደ መደበኛው ስራው እንዲመለስ የተወሰነበትን ምክንያት ዶ/ር መብራቱ አብራርተዋል።
በሚሊኒየም አዳራሽ የነበረው የኮቪድ 19 ህክምና ማዕከል መዘጋቱን ተከትሎ በስሩ የነበሩ የጤና ባለሙያዎችን ዕጣ ፈንታ በተመለከተ የተጠየቁት የማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር፤ ጉዳዩ የሚመለከተው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ መሆኑን በመጠቆም ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል። ተመሳሳይ ጥያቄ የቀረበለት የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የህዝብ ግንኙነት ክፍል፤ በጉዳዩ ላይ መረጃ የሚሰጠው በመጪው ቅዳሜ በሚከናወነው የርክክብ ስነ ስርዓት ላይ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቋል።
በጤና ሚኒስቴር ብሔራዊ የኮቪድ 19 ምላሽ ግብረ ኃይል አስተባባሪ በበኩላቸው በሚሊኒየም አዳራሽ የኮሮና ህክምና ማዕከል ይሰሩ የነበሩ የጤና ባለሙያዎች ቀድሞም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ስር የነበሩ በመሆናቸው “ወደዚያው ይመለሳሉ” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምላሽ ሰጥተዋል። የጤና ሚኒስቴር በተጨማሪነት በኮንትራት የቀጠራቸው የጤና ባለሙያዎችም፤ ኮንትራታቸው ለስድስት ወራት ተራዝሞ ወደ ሌሎች የጤና ተቋማት እንደተዘዋወሩም ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)