በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለአንድ አመት በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር የቆየ አካባቢን የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መልሰው ተቆጣጠሩ

በሃሚድ አወል

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ ካማሺ ዞን፤ ምዥጋ ወረዳ ለአንድ ዓመት ያህል በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር የነበረን አንድ ቀበሌ የመንግስት ጸጥታ ኃይሎች መልሰው ተቆጣጠሩ። የጸጥታ ኃይሎቹ ትላንት ሰኞ ሐምሌ 4፤ 2014 መልሰው የተቆጠጠሩት ዲዴሳ የተባለ ቀበሌን ሲሆን፤ በወረዳው የሚገኙ ሌሎች አምስት ቀበሌዎች ግን አሁንም በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ይገኛሉ ተብሏል። 

ከግንቦት 2013 መጀመሪያ ጀምሮ በጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር የነበረው የዲዴሳ ቀበሌን፤ የመከላከያ ሰራዊት፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ልዩ ኃይል እና ፖሊስ መልሰው የተቆጣጠሩት በትላንትው ዕለት በአካባቢው ከተደረገ ውጊያ በኋላ መሆኑን የምዥጋ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አዛዥ ሻለቃ ጃለታ አየለ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ታጣቂዎቹ ውጊያውን ተከትሎ ይጠቀሙበት የነበረውን ከባድ የጦር መሳሪያ እና ሌሎች “ኋላ ቀር መሳሪያዎችን ጥለው ከአካባቢው መውጣታቸውን” የፖሊስ አዛዡ ገልጸዋል። 

ሻለቃ ጃለታ በትላንትናው ውጊያ የደረሰውን ጉዳት ከመግለጽ ቢቆጠቡም፤ የአካባቢ ነዋሪዎች በታጣቂዎቹ እና በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መካከል የነበረውን የተኩስ ልውውጥ ሸሽተው በጫካ መደበቃቸውን ግን አልሸሸጉም። የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች አካባቢው ወደ ቀድሞው መረጋጋት ለመመለስ በስፍራው አሁንም አሰሳ እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል። 

የዲዴሳ ቀበሌ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እጅ መግባት፤ በምዥጋ ወረዳ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር የሚገኙትን ቀበሌዎች ቁጥር ወደ አምስት እንዲቀነስ አድርጎታል። የምዥጋ ወረዳ ካሉት 12 ቀበሌዎች ውስጥ ግማሽ ያህሉን ለአንድ ዓመት ተቆጣጥረው ከነበሩት የጉህዴን ታጣቂዎች ጋር የክልሉ መንግስት ዕርቅ ለማውረድ ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርግ መቆየቱን የጠቆሙት የወረዳው የፖሊስ አዛዥ፤ ሆኖም ችግሩን በድርድር ለመፍታት የተደረገው ጥረት በመክሸፉ ምክንያት መንግስት እርምጃ ወደ መውሰድ መሸጋገሩን አስረድተዋል።

“[ታጣቂዎቹ] ድርድርን እየተቀበሉ አይደለም። ከተቀበሉ በኋላም አፍርሰዋል። አሁን አማራጭ የለም። እርምጃ ወስዶ ህዝቡን ከዚያ ማውጣት ነው” ሲሉ ሻለቃ ጃለታ መንግስት ኃይል መጠቀምን በመጨረሻ አማራጭነት መወሰዱን ተናግረዋል። የክልሉ መንግስት አሁንም ቢሆን ከታጣቂዎች ጋር ችግሩን በሰላማዊ መንግድ ለመፍታት ፍላጎት እንዳለው የገለጹት የፖሊስ አዛዡ፤ “ [ታጣቂዎቹ] በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን የሚሰጡ ከሆነ መንግስት ይምራል። ሰው እንዲጎዳ አይፈልግም። ወደ ህዝቡ ተቀላቅለው፣ ተሃድሶ ወስደውንም ቢሆን፣ ዕድል ተሰጥቷቸው ይኖራሉ ብለን ነው የምናስበው” ሲሉ አስረድተዋል።

የጉህዴን ታጣቂዎች የዲዴሳ ቀበሌን ተቆጣጥረው በቆዩበት አንድ ዓመት “በህዝብ ላይ በጣም ዘግናኝ እና አጸያፊ የሆነ ነገር” ፈጽመዋል የሚሉት የፖሊስ አዛዡ፤ እርሳቸው ባላቸው መረጃ ብቻ 52 ንጹሃን የአካባቢው ነዋሪዎች መገደላቸውን ገልጸዋል። ታጣቂዎቹ በቀበሌው በተደጋጋሚ ሲፈጽሙት ከቆዩት ግድያ በተጨማሪ የነዋሪዎችን ንብረት ሲዘርፉ እና ሲያወድሙ መቆየታቸውንም አክለዋል።   

ታጣቂዎቹ ባለፈው ዓመት ግንቦት መጀመሪያ የዲዴሳ ቀበሌን ሲቆጣጠሩ “የቀበሌው አመራሮች እንዳለ አፈንግጠው” ወደ ታጣቂዎቹ መግባታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተናገሩት ሻለቃ ጃለታ፤  ቀበሌው ትላንት በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ቢውልም የቀበሌ አመራሮቹ ባለመኖራቸው መንግስታዊ መዋቅር እንዳልነበር አመልክተዋል። በአካባቢው በነበረው የጸጥታ ችግር ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ወደ ጫካ የገቡ ነዋሪዎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እየታሰበ መሆኑን የገለጹት የፖሊስ አዛዡ፤ ህዝቡ ወደ ቀዬው ከተመለሰ በኋላ የቀበሌው መዋቅሮች እንደገና እንደሚደራጁ እና አዳዲስ አመራሮች እንደሚመደቡ ጠቁመዋል። 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተደጋጋሚ ጥቃቶች ከሚደርስባቸው ጥቃቶች አካባቢዎች መካከል የካማሺ ዞን ዋነኛው ነው። በዞኑ ካለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ጀምሮ የሰዓት ዕላፊ ገደብ መጣሉ ይታወሳል።  የእንቅስቃሴ ገደቡ የተጣለው በምዥጋ ወረዳ በተፈጠረ ግጭት የሰዎች ህይወት ማለፉን ተከትሎ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)