ከ32 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፖሊሳዊ ስልጠና የወሰዱ የህክምና ዶክተሮች ሊመረቁ ነው

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መሰረታዊ የፖሊስ ስልጠና የሰጣቸውን የህክምና ዶክተሮች ከ32 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊያስመርቅ ነው። የህክምና ዶክተሮቹ ፖሊሳዊ ስልጠና እንዲወስዱ የተደረገው፤ የፖሊስ ሰራዊትን ባህሪ እንዲረዱ እና ለወደፊቱ ለሚሰጧቸው ግዳጆች ብቁ እንዲሆኑ ታስቦ እንደሆነ ተቋሙ አስታውቋል። 

ለሶስት ወራት ያህል የቆየ ፖሊሳዊ ስልጠና የወሰዱት የህክምና ዶክተሮች ብዛት 16 ሲሆን የምርቃት ስነ ስርዓታቸው የሚከናወነው በሚቀጥለው ሳምንት ቅዳሜ ሐምሌ 16፤ 2014 ነው። በረዳት ኢንስፔክተር ማዕረግ ከሚመረቁት ከእነዚህ የህክምና ዶክተሮች መካከል አስሩ በፌደራል ፖሊስ ሆስፒታል አዲስ የተቀጠሩ ሐኪሞች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ስድስቱ ደግሞ ቀደም ብሎ በሆስፒታሉ ሲሰሩ የነበሩ ናቸው። 

የፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ፍቅሩ ወንዴ፤ ሐኪሞቹ ስልጠናውን እንዲወስዱ የተደረገው “የተቋሙን ባህሪ አውቀው፤ ከተቋሙ የስራ ባህሪ ጋር ግዳጅ ለመሄድ አብሮም ለመንቀሳቀስ” እንዲችሉ በማሰብ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “አብዛኞቹ የፖሊስ ሐኪሞች በአሁኑ ሰዓት ሲቪል ናቸው” የሚሉት ረዳት ኮሚሽነር ፍቅሩ፤ ስልጠናው የህክምና ዶክተሮቹ “ፖሊሱን መስለው፣ ከፖሊሱ ጋር ተዋህደው፣ የፖሊሳዊ ስብዕናውን እና ስነምግባሩን ይዘው እንዲሰሩ” ያስችላቸዋል ብለዋል።

በዚህ እሳቤ መሰረት ላለፉት ሶስት ወራት እንዲሰለጥኑ የተደረጉት የህክምና ዶክተሮች፤ አብዛኛውን ስልጠናቸውን የተከታተሉት በኦሮሚያ ክልል ሰንዳፋ በሚገኘው በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው። ዶክተሮቹ በፖሊስ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በነበራቸው የሁለት ወራት ቆይታ፤ የንድፈ ሐሳብ እና የተግባር ስልጠና መውሰዳቸውን እና ቀሪውን አንድ ወር ደግሞ በአዳማ የመስክ ስልጠና ማዕከል ውስጥ “ፖሊሳዊ የኦፕሬሽን ልምምድ” ማድረጋቸውን የዩኒቨርስቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር ተሻለ ተሾመ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

የፖሊስ ሰራዊትን በሐኪምነት የሚቀላቀሉ የህክምና ዶክተሮች ይወስዱት የነበረው ይህን መሰሉ ፖሊሳዊ ስልጠና ለመጨረሻ ጊዜ የተሰጠው ከ32 ዓመታት በፊት ነበር። ለህክምና ዶክተሮች ይሰጥ የነበረው ፖሊሳዊ ስልጠና ተቋርጦ የቆየው፤ “መደበኛ ፕሮግራም ሆኖ ባለመዘጋጀቱ እና ትኩረት የሚሰጠው አካል በማጣቱ” እንደሆነ ምክትል ኮሚሽነር ተሻለ ተናግረዋል። 

ፖሊሳዊ ስልጠናው “መጀመሪያም ሲጀመር መደበኛ ፕሮግራም ሆኖ በየአመቱ የግድ መቀጠል ያለበት ሆኖ አልነበረም። በተገኘ ጊዜ የሚደረግ እና ሰዎች ባልፈለጉ ጊዜ ደግሞ አስገዳጅ የማይሆንበት ሂደት ስለነበር ለረዥም ጊዜ ተቋርጦ ቆይቷል” ሲሉ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ስልጠናው ላለፉት 32 ዓመታት ያልተካሄደበትን ምክንያት አብራርተዋል። 

“[የፖሊስ] ሰራዊት 24 ሰዓት በሚሰራበት ጊዜ፤ በሰራዊቱ ውስጥ የሚሠሩ ማናቸውም የሲቪልም ይሁን ሌሎች ሰራተኞች እኩል 24 ሰዓት መስራት አለባቸው” የሚሉት የዩኒቨርስቲው ምክትል ፕሬዝዳንት፤ ለዚህ ደግሞ ፖሊሳዊ ስልጠና አስፈላጊ መሆኑን በአጽንኦት ይናገራሉ። ለህክምና ዶክተሮች የሚሰጠው ፖሊሳዊ ስልጠና ቀጣይነት እንዲኖረው፤ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ የስርዓት ትምህርት ቀርጾ በሴኔት ማስጸደቁንም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሪፈራል ሆስፒታል ከዚህ በኋላ አዳዲስ ሐኪሞችን ሲቀጥር ዩኒቨርሲቲው አሰልጥኖ ወደ ተቋሙ እንዲቀላቀሉ ያደርጋል ብለዋል። 

ከ75 ዓመታት በፊት አባ ዲና ፖሊስ ኮሌጅ በሚል ስያሜ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ፤ ከዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት ወደ ዩኒቨርሲቲነት ያደገው ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ላይ ነው። ዩኒቨርስቲው መሰረታዊ ፖሊሳዊ ስልጠና የወሰዱ 16 የህክምና ዶክተሮችን ጨምሮ ከሁለተኛ ዲግሪ እስከ ማዕረግ ሽግግር ትምህርት እና ስልጠና የተከታተሉ 1‚600 ገደማ ተማሪዎችን በመጪው ቅዳሜ ያስመርቃል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)