የ“አል አይን ኒውስ” የኢትዮጵያ ዘጋቢ ሲቪል በለበሱ የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ዋለ

በሃሚድ አወል

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መገናኛ ብዙሃን ለሆነው “አል አይን ኒውስ” በዘጋቢነት የሚሰራው ጋዜጠኛ አልዓዛር ተረፈ ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 7 ከሰዓት በጸጥታ ኃይሎች መያዙን ባለቤቱ እና ባልደረባው ገለጹ። ጋዜጠኛው በጸጥታ አካላት ከተያዘ በኋላ በአዲስ አበባ ላምበረት አካባቢ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዱንም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ጋዜጠኛ አልዓዛር ዛሬ ከቀኑ ሰባት ሰዓት አካባቢ “ሰው ላግኝ” ብሎ ከቤት መውጣቱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የገለጸችው ባለቤቱ ፍቅርተ ተረፈ፤ ከቆይታ በኋላ እጅ ስልኩ ስትደውል እንደማይነሳ እና ቆይቶም አልሰራ እንዳላት አስረድታለች። ከሰዓታት በኋላ የባለቤቷ ጓደኞች አልዓዛር በጸጥታ ኃይሎች ተይዞ ወደ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዱን እንደነገሯት እና በዚያም በአካል አግኝታ እንዳነጋገረችው ገልጻለች።  

አልዓዛርን በታሰረበት ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ የጎበኘው ባልደረባው ዳዊት በጋሻው፤ ጋዜጠኛው የተያዘው ላምበረት መናኸሪያ አካባቢ ከሚገኝ ካፌ እንደሆነ ገልጿል። የሲቪል ልብስ የለበሱ ሁለት ግለሰቦች ጋዜጠኛውን መታወቂያ እንዲያሳያቸው እንደጠየቁት እና “እንፈልግሃለን” ብለው እንደወሰዱት የዓይን እማኞች ነግረውኛል ብሏል። ሁለቱ ግለሰቦች “የፍርድ ቤት ማዘዣ አለማሳየታቸውን” የዓይን እማኞች መግለጻቸውንም አክሏል።

ግለሰቦቹ የጸጥታ ኃይሎች መሆናቸውን የሚገልጽ መታወቂያ እንዲያሳዩት በጋዜጠኛው መጠየቃቸውን ከዓይን እማኞች መስማቱን የተናገረው ዳዊት በጋሻው፤ ይህን ተከትሎም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባልደረባ መሆናቸውን የሚያመለክት መታወቂያ ማሳየታቸውን መረዳቱን አክሏል። ሁለቱ ግለሰቦች አልዓዛርን በያዙበት ወቅት “ለችግኝ ተከላ ጥሩ አመለካከት የለህም፤ ‘ቤተ መንግስት ገብተን፤ በደም የበቀለውን ችግኝ እንነቅላለን’ ብለሃል” በሚል ሲወነጅሉት መሰማታቸውን ጋዜጠኛ ዳዊት ተናግሯል። 

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፎክሎር የመጀመሪያ ዲግሪውን የያዘው ጋዜጠኛ አልዓዛር፤ “አል አይን” የተባለውን መገናኛ ብዙሃን ከመቀላቀሉ በፊት በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በዘጋቢነት ሰርቷል። አልዓዛር በዘጋቢነት እና በአርታኢነት የሚሰራበት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶቹ “አል አይን” በኢትዮጵያ ቢሮውን የከፈተው በ2007 ዓ.ም ነበር። “አል አይን” ከ2011 ጀምሮ በአማርኛ ቋንቋ ዜናዎችን እና ዘገባዎችን በጽሁፍ፣ በምስል እና በቪዲዮ በማቅረብ ላይ ይገኛል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)