የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፤ በመጪው ነሐሴ ወር መጀመሪያ በኬንያ የሚካሄደውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሚታዘበውን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ልዑክ እንዲመሩ ተመደቡ። ክፍለ አህጉራዊው ድርጅት ዶ/ር ሙላቱን ለታዛቢ ልዑክ መሪነት መመደቡን ያስታወቀው ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 7 ባወጣው መግለጫ ነው።
የኢጋድ ዋና ጸሀፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ውሳኔውን ይፋ ባደረጉበት መግለጫቸው፤ ዶ/ር ሙላቱ “በጣም የተከበሩ የሀገር መሪ፣ ልምድ ያላቸው ዲፕሎማት ናቸው” በማለት አሞግሰዋቸዋል። ዋና ጸሀፊው በዚሁ መግለጫቸው “የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ልዑክን ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በመምራታቸው ኩራት ይሰማናል” ብለዋል።
ኢጋድ በመጪው ነሐሴ 3፤ 2014 የሚካሄደውን የኬንያ ምርጫ የሚታዘበው፤ በኬንያ የምርጫ እና የድንበር ገለልተኛ ኮሚሽን በቀረበለት ግብዣ ነው። ተመሳሳይ ግብዣ የቀረበለት የአውሮፓ ህብረት፤ የኬንያን የምርጫ ሂደት የሚከታተሉ ባለሙያዎችን እና ታዛቢዎችን ከሁለት ሳምንት በፊት ማሰማራቱ ይታወሳል። በዘንድሮው የኬንያ ምርጫ በአሁኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና በቀድሞው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ መካከል ከፍተኛ የምረጡኝ ፉክክር እየተደረገ ይገኛል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)