የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ የሙከራ ስርጭት ሊጀምር ነው

በሃሚድ አወል

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የራሱን የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ አቋቋሞ ከ15 ቀናት በኋላ የሙከራ ስርጭቱን ሊጀምር ነው። የክልሉ መንግስት የቴሌቪዥን ጣቢያውን ለማደራጀት ወደ 150 ሚሊዮን ብር ገደማ ማውጣቱን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል።

“የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሚዲያ” የሚል ስያሜ የሚኖረው የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ የሙከራ ስርጭቱን የሚጀምረው ለጊዜው በቀን ለስድስት ሰዓታት ብቻ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ መለሰ ሰንበታ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ይህ እንዲሆን የተደረገው ኤጀንሲው አሁን ባለው የሰው ኃይል እና አደረጃጀት የ24 ሰዓት ስርጭት በአንዴ ለማስተላለፍ “የአቅም እጥረት ሊያጋጥመው ይችላል” በሚል ስጋት መሆኑን አቶ መለሰ አስረድተዋል። 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ በአጠቃላይ ሁለት መቶ ሰራተኞች በስሩ አሉ። ኤጀንሲው ከክልሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ተነጥሎ ራሱን ችሎ በአዋጅ የተቋቋመው በ2005 ዓ.ም ነው። የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ በአሁኑ ወቅት ከብሔራዊው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በሳምንት ለሶስት ቀናት የአየር ሰዓት ገዝቶ ስርጭቶችን እያስተላለፈ ይገኛል።

ሰኞ፣ ረቡዕ እና አርብ ከረፋድ 4፡30 እስከ 5 ሰዓት ባለው ጊዜ በሚተላለፈው በዚህ ስርጭት፤ በዋነኛነት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን የተመለከቱ ዜናዎች እና ፕሮግራሞች ይቀርቡበታል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለዚህ ስርጭት በዓመት 600 ሺህ ብር ገደማ ለብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያው እንደሚከፍል አቶ መለሰ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ “የክልሉን ነዋሪ መረጃ የማግኘት ፍላጎት እና መብት ለማሟላት” በሚል እሳቤ የራሱን የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ ለማቋቋም ወስኖ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የገባው ባለፈው 2013 ዓ.ም. ነው። በዚህም መሰረት ኤጀንሲው ዓለም አቀፍ ጨረታ አውጥቶ የካሜራ እና የስርጭት ቁሳቁሶች ግዢዎችን መፈጸሙን ምክትል ስራ አስኪያጁ አመልክተዋል። 

ከተወሰኑ ካሜራዎች በስተቀር የተገዙት ዕቃዎች ሀገር ውስጥ መግባታቸውን የጠቆሙት አቶ መለሰ፤ በአሁኑ ወቅት የተከላ እና የማዋቀር ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። የጣቢያውን የስቱዲዮ ዕቃዎች ያቀረበው እና ገጠማ በማከናወን ላይ የሚገኘው Broadcast and Studio Solutions (BSS) Trading የተሰኘ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ድርጅት መሆኑንም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ከድርጅቱ ጋር የገባው ስምምነት ዕቃዎቹን፤ ከማቅረብ እና ከመግጠም ባሻገር ባለሙያዎችን ማሰልጠንንም ያካትታል። በዚህም መሰረት አዲስ የተቋቋመው የክልሉ የቴሌቪዥን ጣቢያ የቴክኖሎጂ ክፍል ሰራተኞች ከ20 እስከ 28 ቀናት የሚደርስ ስልጠና በድርጅቱ ይሰጣቸዋል። 

አዲሱ የቴሌቪዥን ጣቢያ የሙከራ ስርጭቱን ከ15 ቀናት በኋላ ሲጀምር ፕሮግራሞቹን የሚያስተላልፈው በአማርኛ ቋንቋ ይሆናል። ጣቢያው አቅሙን ካደራጀ በኋላ በክልሉ በሚነገሩ ሌሎች ቋንቋዎች እንዲሁም በአረብኛ ቋንቋ ዜና እና ፕሮግራሞች ማሰራጨት እንደሚጀምር አቶ መለሰ ገልጸዋል።

የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያው የሙከራ ስርጭቱን ከጀመረ በኋላ ባሉት ሁለት እና ሶስት ወራት፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገጽታን እንዲሁም ራሱ ሚዲያውን የማስተዋወቅ ስራ ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ምክትል ስራ አስኪያጅ አስረድተዋል። የቴሌቪዥን ጣቢያው ወደ መደበኛ ስርጭት ሲገባ የሚያስተላልፋቸው 32 የፕሮግራም አይነቶች መለየታቸውን የጠቆሙት ምክትል ስራ አስኪያጁ፤ ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ አስራ አምስቱ ፕሮግራሞች “ባክሎግ” በመሰራት ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።  

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የቴሌቪዥን ጣቢያ ስራ ሲጀምር፤ በኢትዮጵያ የህዝብ ብሮድካስት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቁጥር ወደ 11 ያድጋል። በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን መረጃ መሰረት ከጋምቤላ፣ ሲዳማ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች በስተቀር ሁሉም ክልሎች የራሳቸው የሳተላይት የቴሌቪዥን ስርጭት አላቸው። 

ተጠሪነታቸው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆኑት፤ የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞችም እንዲሁ የየራሳቸውን የቴሌቪዥን ጣቢያ አቋቁመው ዜና እና ፕሮግራሞችን በሳተላይት በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ። ስርጭቱን በሳተላይት አማካኝነት በማስተላለፍ ላይ የሚገኘውና በትግራይ ክልላዊ መንግስት የሚተዳደረው ትግራይ ቲቪ፤ በቀድሞው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በአሁኑ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ተሰጥቶት የነበረው ፍቃድ ባለፈው ዓመት መጀመሪያ ላይ መሰረዙ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)