ከኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ስር በዋሉ 8 ግለሰቦች ላይ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

በሃሚድ አወል

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉ ስምንት ግለሰቦች ላይ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ በፍርድ ቤት ተፈቀደ። የምርመራ ጊዜውን የፈቀደው ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 11፤ 2014 የዋለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው። 

ችሎቱ የምርመራ ጊዜውን የፈቀደው የፌደራል ፖሊስ እና የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ባለፈው ሳምንት አርብ ሐምሌ 8፤ 2014 ያደረጉትን ክርክር ከመረመረ በኋላ ነው። የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ በዛሬው ውሎው የተጠርጣሪዎቹ በዋስትና መውጣት “ምርመራው የተፈለገውን ውጤት እንዳያስገኝ ሊያደርግ ስለሚችል” በሚል ጠበቆች ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አድርጓል። 

ፍርድ ቤቱ ከዚህ በተጨማሪም መርማሪ ፖሊስ አሰባስባቸዋለሁ ያላቸውን ማስረጃዎች እንዲያሰባስብ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜን ፈቅዷል። ለፖሊስ የተሰጠው የምርመራ ጊዜ ካለፈው ሳምንት አርብ ሐምሌ 8 ጀምሮ የሚታሰብ ነው።

የአዲስ አበባ ቴክኒክ ሙያ ስልጠና እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ምክትል  ኃላፊ አቶ አብርሃም ሰርሞሎን ጨምሮ ስምንት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፈው ረቡዕ ሐምሌ 6፤ 2014 ነበር። ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ከ10 ቀናት በፊት ሐምሌ 1፤ 2014 በተካሄደው የኮንዶሚኒየም ዕጣ ስነ ስርዓት ላይ፤ ለዕጣው ብቁ ያልሆኑ ሰዎች እንዲካተቱ አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው ነው።

ስምንቱም ተጠርጣሪዎች ዛሬ ጉዳያቸውን በችሎት ተገኝተው ተከታትለዋል። ዛሬ ችሎት ፊት ከቀረቡት ግለሰቦች መካከል አራቱ የሶፍትዌር ባለሙያዎች ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)