የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለ2015 በጀት ዓመት 3.2 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው ገለጸ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ2015 በጀት ዓመት የያዛቸውን ዕቅዶች ለማስፈጸም 3.2 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው አስታወቀ። ኮሚሽኑ ከዚህ በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ ለሚያከናውናቸው ተግባራት የሚውል 208.6 ሚሊዮን ብር ከተለያዩ የልማት አጋሮች ለማሰባሰብ ማቀዱንም ገልጿል። 

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ይህን ያስታወቀው ትላንት ማክሰኞ ሐምሌ 12፤ 2014 ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስተባባሪ እና አማካሪ ኮሚቴ ባቀረበው የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ነው። በ35 ገጾች የተዘጋጀው የዕቅድ ሰነዱ፤ ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ ያቀዳቸውን ቁልፍ ተግባራት፣ በዕቅድ አፈጻጸም ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች እና መፍትሔዎችን ጨምሮ ሌሎችን ጉዳዩችንም አካትቷል።

የምክክር ኮሚሽኑ ከያዝነው ሐምሌ ወር ጀምሮ ሊያከናውናቸው ያቀዳቸው ቁልፍ ተግባራት በቁጥር 18 እንደሚደርሱ በሰነዱ ላይ ተመልክቷል። ከእነዚህ ቁልፍ ተግባራት ውስጥ የምክክር ተሳታፊዎችን መለየት እና የምክክር አጀንዳዎችን ማሰባሰብና መቅረጽ ይገኙበታል። የሀገራዊ ምክክር መድረኩን የሚያከናውኑ ሰብሳቢዎችን፣ አወያዮችና ቃለ-ጉባኤ ያዦችን መለየት፣ መምረጥ እና ወደ ትግበራ ማስገባት ሌላው በቁልፍ ተግባርነት የተቀመጠ ጉዳይ ነው። 

በ2015 በተለያዩ ደረጃዎች በተለዩ አጀንዳዎች ላይ ሀገራዊ ምክከር ለማከናወን ያቀደው ኮሚሽኑ፤ ወደዚህ ስራ ከመግባቱ በፊት የኮሚሽኑን ዋና እና ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን ማደራጀት እንዲሁም የበጀት እና ሀብት አጠቃቀምን የማሳደግ ተግባራትን እንደሚያከናውን በሰነዱ ሰፍሯል። ከሰባት ወራት በፊት በአዋጅ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስካሁን ሲጠቀም የቆየው በጀት፤ ለእርቀ ሰላም እንዲሁም ለአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽኖች ተመድቦ የነበረውን ነው።

ከሶስት ዓመት በፊት ተቋቁመው ባለፈው የካቲት ወር የፈረሱት ሁለቱ ኮሚሽኖች፤ ለ2014 በጀት ዓመት የተመደበላቸው 47 ሚሊዮን ብር ገደማ ነበር። ከዚህ ውስጥ 25.7 ሚሊዮን ብሩ ተመድቦ የነበረው ለአስተዳደር ወሰን እና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ሲሆን፤ ቀሪው 21.4 ሚሊዮን ብር የተበጀተው ደግሞ ለእርቀ ሰላም ኮሚሽን ነው። 

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ለ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ማስፈጸሚያ ከመንግስት እንዲመደብለት የሚጠብቀው የገንዘብ መጠን 3.2 ቢሊዮን ብር መሆኑን ለተወካዮች ምክር ቤት አስተባባሪ እና አማካሪ ኮሚቴ በቀረበው ሰነድ ላይ ሰፍሯል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕ/ር መስፍን አርዓያ፤ በበጀት ዝግጅት ወቅት ለኮሚሽኑ ያስፈልገዋል በሚል ተይዞ የነበረው በጀት 4 ቢሊዮን ብር እንደነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ፕ/ር መስፍን “የሀገሪቱን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የመጨረሻውን ዝቅተኛ በጀት ነው ያወጣነው” ሲሉ ኮሚሽኑ ለገንዘብ ሚኒስቴር ሊያቀርበው የተዘጋጀው የበጀት ጥያቄ በርካታ ነገሮችን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ አስረድተዋል። “ይሄ ገንዘብ ለሀገራዊ ስራ ስለሆነ፤ ያን ያህል የሚያስደነግጥ አይደለም” ሲሉም የበጀት ጥያቄው በገንዘብ ሚኒስቴር ተቀባይነት ያገኛል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል። 

ከአስራ አንዱ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች አንዱ የሆኑት ዶ/ር ዮናስ አዳዬ፤ “[በጀቱ] የሀገራችንን የኢኮኖሚ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ወጪዎችን እጅግ በጣም ቀንሶ የተዘጋጀ ነው” ሲሉ የፕ/ር መስፍንን ሀሳብ ተጋርተዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከመንግስት ለማግኘት ካቀደው በጀት በተጨማሪ ከኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች እና ከውጭ ተቋማት ተጨማሪ ገንዘብ የማሰባሰብ እቅድ እንዳለው ለተወካዮች ምክር ቤት አስተባባሪ እና አማካሪ ኮሚቴ ባቀረበው ሰነድ ላይ አመልክቷል።  

ሀገራዊ የምክከር ኮሚሽኑ ይህ ዕቅድ ቢኖረውም፤ ከመንግስት በስተቀር ከሌሎች አካላት ገንዘብ በቀጥታ እንደማይቀበል ፕ/ር መስፍን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “በቀጥታ ወደ እኛ ገንዘብ እንደሚመጣ አንፈልግም። ሌሎች እንኳን [ገንዘብ] ቢሰጡን ቋት የፈጠርነው ገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ ነው” ሲሉ ገንዘቡ በቀጥታ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቋት ከገባ በኋላ ኮሚሽኑ ገንዘቡን ላቀደው ተግባር ወስዶ እንደሚጠቀም አብራርተዋል።  

“በተለይ የውጭዎቹ ገንዘብ ይሰጡ እና አብሮ ብዙ ኮተት ስለሚመጣ ያንን አንፈልግም። እጅ መጠምዘዝ አንፈልግም፤ መታዘዝ አንፈልግም”

ፕ/ር መስፍን አርዓያ- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር

ፕ/ር መስፍን “በተለይ የውጭዎቹ ገንዘብ ይሰጡ እና አብሮ ብዙ ኮተት ስለሚመጣ ያንን አንፈልግም። እጅ መጠምዘዝ አንፈልግም፤ መታዘዝ አንፈልግም” ሲሉ የምክክር ኮሚሽኑ ከመንግስት ውጪ ከሌሎች አካላት በቀጥታ ገንዘብ ለመቀበል የማይፈልግበትን ምክንያት አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)