ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) በጠየቀችው የተራዘመ የብድር አቅርቦት (Extended Credit Facility) ላይ በ2015 ዓ.ም. የመጀመሪያ ወራት ድርድር ሊጀመር እንደሚችል ተቋሙ ፍንጭ ሰጠ። ድርጅቱ በሳምንቱ መጀመሪያ ከኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴ ጋር በተደረገ ስብሰባ ላይ ለሀገሪቱ “አዲስ የተራዘመ የብድር አቅርቦት ስምምነት ለማጽደቅ ያስፈልጋሉ” ያላቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ዘርዝሯል።
ፈረንሳይ እና ቻይና በተባባሪ ሊቀመንበርነት በሚመሩትን ባለፈው ሰኞ ሐምሌ 11፤ 2014 በተካሄደው የኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የተገኘው፤ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ ለማቅረብ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስልጣን ሲይዙ፤ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከተፈራረመቻቸው ሁለት ስምምነቶች አንዱ ከተቋሙ የተራዘመ የብድር አቅርቦት ማግኘት ነበር።
ኢትዮጵያ ከአይ ኤም ኤፍ ለመበደር የተስማማችው 2.9 ቢሊዮን ዶላር የብድር ጊዜ እስከ 2015 ዓ.ም. የሚዘልቅ ነበር። ይሁንና ይህ ስምምነት፤ ኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ለማድረግ አቅርባ የነበረው ጥያቄ በመዘግየቱ ምክንያት ባለፈው መስከረም ወር ተቋርጧል።
ኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈሏን ለማሸጋሸግ ጥያቄ ያቀረበችው ለቡድን 20 አገራት የጋራ ማዕቀፍ ነበር። በወቅቱ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ሌሎች ሁለት ሀገሮች ተመሳሳይ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል። በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ጦርነት፤ ሀገሪቱ በዕዳ አከፋፈል ማሻሻያው ላይ የምታደርገውን ድርድር አወሳስቦባት ቆይቷል።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ድርድሩን በቅርበት የሚከታተሉ የፋይናንስ ባለሙያ፤ ባለፈው ሰኞ በተካሄደው የአበዳሪዎች ኮሚቴ ስብሰባ ላይ አይ ኤም ኤፍ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ይዞታ በተመለከተ ያቀረበው ማብራሪያ ለሂደቱ “አዎንታዊ ሚና” ሊኖረው ይችላል ይላሉ። ባለሙያው እንደሚሉት ሶስተኛው የኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴ ስብሰባ ተጨባጭ ለውጥ የሚታይበት ሊሆን ይችላል።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በሁለተኛው የአበዳሪዎች በስብሰባ ባቀረበው እና “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው ሰነድ፤ አይ ኤም ኤፍ ኢትዮጵያን ለመደገፍ “ቁርጠኛ መሆኑን” ይገልጻል። ሆኖም ድጋፉ በተጨባጭ ተግባራዊ የሚሆንበት የጊዜ ሰሌዳ በተቋሙ አስተዳደር እና ሰራተኞች እንደማይወሰን በሰነዱ ላይ ተመላክቷል።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት በመስከረም 2014 ያቀረበው አዲስ የብድር ስምምነት ጥያቄ በፍጥነት ምላሽ ለማግኘት፤ የለጋሾች ማረጋገጫ እና የአይ ኤም ኤፍ የስራ አስፈጻሚ ቦርድን ድጋፍ ይፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ ለዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ከኢትዮጵያ አበዳሪዎች የፋይናንስ ማረጋገጫ ማግኘት ይኖርበታል።
በአይ ኤም ኤፍ ሰነድ ላይ “ቀሪ ስራዎች” ተብለው የተጠቀሱ ጉዳዮች፤ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በቅርብ የተከሰቱ ለውጦችን ማካተት፣ የፋይናንስ ፍላጎቶችን መለየት፣ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የዕዳ ዘላቂነት ትንተና ማከናወን እና የፋይናንስ ክፍተቶች እንዴት እንደሚሞሉ ከለጋሾች ጋር መወያየት ናቸው። የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ጋር የሚፈራረመውን ስምምነት ማዘጋጀት ሌላው በቀጣይ የሚጠበቅ ሂደት ነው። ይህ ውል በአይ ኤም ኤፍ የስራ አመራር ቦርድ መጽደቅ ይጠበቅበታል።
አይ ኤም ኤፍ ለኢትዮጵያ አዲስ የተራዘመ የብድር አቅርቦት (ECF) ለማዘጋጀት ያቀደው በመጪው መስከረም 2015 ላይ ነው። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ያወጣው የጊዜ ሰሌዳ እንደሚያሳየው የመጨረሻው ስምምነት ከመደረጉ አስቀድሞ ወደዚያው የሚመራ ድርድር ይካሄዳል።
አይ ኤም ኤፍ ከስምምነት አስቀድሞ ድርድር ይካሄዳል ቢልም “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ባለሙያ ግን ስምምነቱ ጸድቆ በታቀደው ጊዜ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ይጠብቃሉ። ባለሙያው ለዚህ እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቅሱት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በሀገሪቱ ላያ ሳደረው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ቀደም ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር የተፈራረማቸው ስምምነቶች፤ የብር የመግዛት አቅምን ማዳከምን ጨምሮ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የተለያዩ ማሻሻያዎች አስከትሏል። ማሻሻያዎቹ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ብርቱ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን የሚያስታውሱት የፋይናንስ ባለሙያ፤ አዲሱ ስምምነት “ምን ይዞ ይመጣል?” የሚል ስጋት አላቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)