በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር በፌደራል መንግስት እና በትግራይ ክልል መካከል ሊደረግ በታቀደው ድርድር ላይ ለመወያየት ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው። አምባሳደሩ በአዲስ አበባ ቆይታቸው በታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ጭምር ውይይት ያደርጋሉ።
ማይክ ሐመር ወደ አዲስ አበባ የሚያቀኑት ከነገ ሐምሌ 17 እስከ ሐምሌ 25፤ 2014 ባሉት ጊዜያት እንደሚሆን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ዛሬ ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። አምባሳደሩ በዚህ ጉዟቸው ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ግብጽ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችን ይጎበኛሉ ተብሏል።
የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑኩ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ በትግራይ ክልል እና በፌደራል መንግስት ባለስልጣናት መካከል ሊደረግ የታቀደውን ድርድር ወደ ፊት ለማራመድ የሚደረገውን ጥረት “የመገምገም እድል” እንደሚኖራቸው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መግለጫ ጠቁሟል። አሜሪካ “ለሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች አካታች ፖለቲካዊ ሂደት፣ ዘላቂ ሰላም፣ ጸጥታ እና ብልጽግና ለመፍጠር የሚደረግ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለማራመድ ቁርጠኛ ነች” ሲል የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ የሀገሪቱን አቋም አስታውቋል።
ማይክ ሐመር በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከሚያተኩሩባቸው ጉዳዮች መካከል የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ሂደት እና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች የፈጸሙ ተጠርጣሪዎችን ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገኝበት በዛሬው መግለጫ ተመልክቷል። የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑኩ ከዚህ በተጨማሪም በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል ላለው ልዩነት ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት የአሜሪካንን ድጋፍ ያቀርባሉ ተብሏል።
አምባሳደር ሐመር ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው አስቀድሞ የህዳሴው ግድብን ጨምሮ በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ከሆኑት ዶ/ር ስለሺ በቀለ ጋር ተገናኘተው መነጋገራቸው ይታወሳል። ዶ/ር ስለሺ በአምባሳደርነት ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ከመሄዳቸው በፊት የህዳሴ ግድብ ዋና ተደራዳሪ እንዲሆኑ በኢትዮጵያ መንግስት ተሹመው እንደነበር አይዘነጋም።
አምባሳደር ስለሺ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅትም የህዳሴው ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ ከሱዳን እና ግብጽ ጋር በምታደርጋቸው ድርድሮች ላይ ቁልፍ ሚና ሲጫወቱ የነበሩ ናቸው። በሶስቱ ሀገራት መካከል የሚደረገውን ድርድር ሲመራ የቆየው የአፍሪካ ህብረት ነው። የአሜሪካ ልዩ ልዑክ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከህብረቱ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ማይክ ሐመር፤ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ተደርገው የተሾሙት ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ነበር። ሐመር የልዩ ልዑክነት ሹመት ካገኙ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጡት ባለፈው ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። ልዩ ልዑኩ በሰኔ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)