የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት “ለቀጣዩ ዓመት ስራዎቼ 30 ሚሊዮን ብር ያስፈልገኛል” አለ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በ2015 በጀት ዓመት ለሚያከናውናቸው ተግባራት 30 ሚሊዮን ብር ገደማ እንደሚያስፈልገው አስታወቀ። የጋራ ምክር ቤቱ በበጀት ዓመቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አቅም የመገንባት፣ በሀገራዊ ምክክር እንዲሁም በአካባቢ ምርጫ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ የማድረግ ዕቅድ እንዳለው ገልጿል። 

የጋራ ምክር ቤቱ የበጀት ፍላጎቱን ያስታወቀው ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 18፤ 2014 በአዲስ አበባው ኢንተርሌግዠሪ ሆቴል ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነው። ምክር ቤቱ በዛሬው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የ2015 በጀት ዓመት ዕቅዱን ለአባል የፖለቲካ ድርጅቶቹ አቅርቧል። በዚህ ዕቅድ ላይ ምክር ቤቱ ያስፈልገኛል ያለው አጠቃላይ ግምታዊ በጀት እና የገንዘብ ምንጮች ይፋ ቢደረጉም፤ የትኞቹ ተግባራት በምን ያህል ገንዘብ እንደሚከናወኑ በዝርዝር አልተቀመጠም።   

ከአንድ ወር በፊት የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሆነው የተመረጡት ዶ/ር መብራቱ አለሙ፤ ይህ የሆነበት ምክንያት ዝርዝሩን የመስራት ኃላፊነት የተጣለበት በምክር ቤቱ ስር ያለው የአስተዳደር እና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ በመሆኑ ነው ብለዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ በዛሬው ስብሰባው አስተዳደር እና ፋይናንስን ጨምሮ የስድስት ቋሚ ኮሚቴዎች አባላት ምርጫ አካሂዷል። 

ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ 53 አባል ፓርቲዎች በጋራ ያቋቋሙት ምክር ቤቱ፤ ለ2015 በጀት የሚያስፈልገውን ገንዘብ በዋናነት ለማግኘት ያቀደው ከዓለም አቀፍ ለጋሽ አካላት ነው። ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚሰጥ ድጋፍ፣ ከመንግስታዊ ድርጅቶች የሚገኝ ገንዘብ እና የአባላት መዋጮም በምክር ቤቱ በበጀት ምንጭነት ተይዘዋል። 

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ፤ በበጀት ዓመቱ የሚያደርጋቸው ስብሰባዎች ሙሉ ወጪ በአንድ የኔዘርላንድ ተቋም ይሸፈናሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ዶ/ር መብራቱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከ22 ዓመታት በፊት በሰባት የኔዘርላንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተቋቋመው፤ የኔዘርላንድ የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲ ተቋም የጋራ ምክር ቤቱ ከዚህ በፊት ሲያደርጋቸው የነበሩ ስብሰባዎችን ሙሉ ወጪ ሲሸፍን መቆየቱን የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አስታውሰዋል። 

የጋራ ምክር ቤቱ ከምርጫ እና ከበይነ ፓርቲ ውይይቶች ጋር በተያያዘ ለሚያደርጋቸው ክንውኖች የሚያስፈልገውን የገንዘብ መጠን ለማግኘት ያቀደው ከምርጫ ቦርድ ነው። ዶ/ር መብራቱ “ምርጫ ቦርድ የሚያግዘን እና ወጪዎችን የሚሸፍን ይመስለኛል” ይላሉ። 

ከሶስት ዓመት በፊት በ2011 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፤ ከአባል የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰበሰብ ወርሃዊ መዋጮን ለምክር ቤቱ በተጨማሪ የገቢ ምንጭነት ይጠቀማል። በምክር ቤቱ ደንብ መሰረት እያንዳንዱ አባል ፓርቲ በወር 500 ብር ወርሃዊ ክፍያ የመፈጸም ግዴታ አለበት።

ለወርሃዊ ክፍያ የተመደበው የገንዘብ መጠን አነስተኛ ቢሆንም፤ በአብዛኛው የምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች ዘንድ ግን ይህንኑ ተግባራዊ ማድረግ ላይ “ቸልተኝነት እንደሚስተዋል” በዛሬው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተነስቷል። የጋራ ምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ዶ/ር አለሙ ስሜ “ጥቂት ፓርቲዎች ናችሁ ይሄን ግዴታችሁን የምትወጡት” ሲሉ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ የተገኙ የምክር ቤቱን አባል ፓርቲዎች ወቅሰዋል። 

ዶ/ር አለሙ አክለውም ክፍያው “የጋራ ምክር ቤቱን መፈለጋችንን የሚያመላከት commitment መገለጫ ነው እንጂ፤ ያቺ አምስት መቶ ብር ከ53 ፓርቲ መጥታ በወር ይህን ስራ ታሰራናለች የሚል [ግምት] የለንም” ሲሉ ተደምጠዋል። የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሉ ዶ/ር አለሙ “በሚቀጥለው ጠቅላላ ጉባኤ ስንጠራ፤ ያልከፈሉት የጉባኤ ተሳታፊ እንደማይሆኑ ከወዲሁ መታወቅ አለበት” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢም በተመሳሳይ “ቀጣይ ስብሳባዎች ሲኖሩን ይህንን ክፍያ ያልፈጸሙ ፓርቲዎችን ላለመጋበዝ በስራ አስፈጻሚ ወስነናል” በማለት የዶ/ር አለሙን ሃሳብ አጠናክረዋል። የአባል የፖለቲካ ፓርቲዎች ወርሃዊ ክፍያን አስመልክቶ በቀረበው ወቀሳ እና ማስጠንቀቂያ ላይ በዛሬው ጠቅላላ ጉባኤ ከተገኙ ፓርቲዎች የተሰጠ አስተያየት የለም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)