የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር ከእስር ተፈቱ

በሃሚድ አወል

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን “አመጽ ለማነሳሳት ሞክረዋል” በሚል ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) ሊቀመንበር አቶ ግራኝ ጉደታ ከእስር ተፈቱ። ለ50 ቀናት ገደማ በእስር ላይ የቆዩት አቶ ግራኝ የተለቀቁት ባለፈው አርብ ሐምሌ 15፤ 2014 ነው። 

የጉሕዴን ሊቀመንበር በካማሺ ከተማ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ልዩ ኃይል አባላት የተያዙት ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ነበር። ሊቀመንበሩ ለእስር የተዳረጉት፤ በካማሺ ዞን ምዥጋ ወረዳ በጉሕዴን ታጣቂዎች እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጸጥታ ኃይሎች መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ 19 ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው።

አቶ ግራኝ ጉደታ በፖሊስ ከተያዙ በኋላ ለመጀመሪያዎቹ 10 ቀናት እንዲቆዩ የተደረጉት በካማሺ ከተማ በሚገኝ የወጣቶች ማዕከል ውስጥ ነበር። ከዚያ በኋላ ወደ ካማሺ ከተማ ማረሚያ ቤት የተዘዋወሩት የጉሕዴን ሊቀመንበር፤ ለሶስት ጊዜ ፍርድ ቤት ቢቀርቡም የክልሉ ፖሊስ በእርሳቸው ላይ ማስረጃ ማግኘት ባለመቻሉ ምክንያት ከእስር መፈታታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የንቅናቄውን ሊቀመንበር ከእስር መፈታት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጡት የካማሺ ከተማ ከንቲባ አቶ አብደታ ደሬሳ፤ አቶ ግራኝ የተለቀቁት “በክልሉ እየተሰራ ያለውን የጸጥታ ስራ ለማሳለጥ ያግዛል” በሚል ምክንያት እንጂ “ማስረጃ በማጣት አይደለም” ሲሉ አስተባብለዋል። ለጸጥታ ስራው “ትኩረት ለመስጠት [በማሰብ] እና እርሳቸው ከእስር የሚለቀቁ ከሆነ ትልቅ ስራ ለመስራት ስለሚቻል በሚል ክልሉ ከእስር ቤት እንዲወጡ አድርጓል” ሲሉ ከንቲባው ተናግረዋል። 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ባለፈው መጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ከጉሕዴን ታጣቂዎች ጋር ዕርቅ በፈጸመበት ወቅት ንቅናቄውን በሊቀመንበርነት የሚመሩት አቶ ግራኝ ጉልህ ሚና ነበራቸው። ይፋዊ የዕርቅ ስነ ስርዓት ከተፈጸመ በኋላ ከነትጥቃቸው ወደ ምዥጋ ወረዳ እንዲገቡ የተደረጉ የጉሕዴን ታጣቂዎች ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ከተጋጩ በኋላ ግን አቶ ግራኝ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል። 

የካማሺ ከተማ ከንቲባ የጉህዴን ሊቀመንበር በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የተደረገበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ “ዕርቁ በጥቂት ሰዎች ወደ ኋላ ሲመለስ ‘ይህን እርቅ ያልተቀበሉ አካላት ነበሩ’ በሚል ለእርሳቸው ደህንነት ሲባል መንግስት አቅጣጫ አስቀምጦ ማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ተደርጎ ነበር” ብለዋል። ይህን የከንቲባውን ገለጻ የማይቀበሉት አቶ ግራኝ በበኩላቸው “የታሰርኩት ‘ዕርቁን አልተቀበለም’ በሚል ጥርጣሬ ነው” ባይ ናቸው። “ ‘ዕርቁን አልተቀበልክም’ አሉኝ። እንዴት ነው ባልቀበለው ኖሮ ይሄንን ያህል መስዋትነት የምከፍለው?” ሲሉ ጥያቄ አዘል መከራከሪያ ያቀርባሉ። 

አቶ ግራኝ ከዚህ በተጨማሪም “ለታጣቂዎች ስልክ ደውለሃል” የሚል ውንጀላ እንደቀረበባቸው ያስረዳሉ። ለጉሕዴን ታጣቂዎች ስልክ መደወላቸውን የሚያምኑት አቶ ግራኝ፤ “አይደለም እኔ [የክልሉ] ምክትል ፕሬዝዳንት አብረው እየተደዋወሉ ነው። እኔ ስልክ የምደውለው፤ ወደ ሰላም ያልመጡ ልጆች ወደ ሰላም እንዲመጡ ነው” ሲሉ ከስልክ ንግግራቸው ጀርባ አለ ያሉትን ምክንያቱን ያብራራሉ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት በክልሉ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች “የጉሕዴን ታጣቂዎች” የሚላቸውን አካላት በተደጋጋሚ ይወነጅላል። የክልሉ መንግስት በጫካ የሚገኙ የጉሕዴን ታጣቂዎችን ወደ ዕርቅ ሂደት የማምጣት ፍላጎት አሁንም እንዳለው የካማሺ ከተማ ከንቲባ አቶ አብደታ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የዕርቅ ሂደቱን ተከትሎም የክልሉ መንግስት የሰላም እና ጸጥታ ሁኔታው ቀድሞ ወደነበረበት እንዲመለስ እና ከቀያቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ የማድረግ ዕቅድ እንዳለውም አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)