በሃሚድ አወል
የገቢዎች ሚኒስቴር በትግራይ ክልል ለተመዘገቡ 87 የክልል እና የፌደራል ግብር ከፋዮች ጊዜያዊ የታክስ ክሊራንስ የምስክር ወረቀት ሰጠ። በክልሉ ከተመዘገቡ 11 ግብር ከፋዮችም 15.9 ሚሊዮን ብር ውዝፍ የግብር ዕዳ መሰብሰቡን አስታውቋል።
በትግራይ ክልል የተመዘገቡ ግብር ከፋዮች ጊዜያዊ የታክስ ክሊራንስ ማግኘታቸው ግብር እንዲከፍሉ፣ ብድር እንዲያገኙ፣ በጨረታ እንዲሳተፉ እና የተሽከርካሪ እንዲሁም የኮንስትራክሽን መሳሪያዎች እድሳት እንዲያከናውኑ ያስችላቸዋል። ግብር ከፋዮቹ ጊዜያዊ ክሊራንስ ያገኙት፤ ባለፈው ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ የገንዘብ ሚኒስቴር “ጊዜያዊ የአሰራር ስርዓት” እንዲዘረጋ ለገቢዎች ሚኒስቴር ደብዳቤ ደብዳቤ መጻፉን ተከትሎ ነው።
የገንዘብ ሚኒስቴር ደብዳቤውን ከጻፈ በኋላ፤ የገቢዎች ሚኒስቴር በአዲስ አበባ የሚገኘውን የሰሜን ምዕራብ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱን በትግራይ ክልል የተመዘገቡ ግብር ከፋዮችን እንዲያስተናግድ መመደቡን የቅርንጫፉ ስራ አስኪያጅ አቶ ቶሉ ፊጤ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የሰሜን ምዕራብ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ለትግራይ ግብር ከፋዮች አገልግሎት መስጠት የጀመረው ከአንድ ወር ገደማ በፊት ሰኔ 24፤ 2014 ጀምሮ ነው።
በገንዘብ ሚኒስቴር ውሳኔ መሰረት ቅርንጫፉ ለግብር ከፋዮቹ መስጠት የሚጠበቅበት አገልግሎት፤ ጊዜያዊ የታክስ ክሊራንስ መስጠት፣ ያልከፈሉት ውዝፍ ግብር ዕዳ ካለ መሰብሰብ እና የስራ ቦታቸውን መቀየር ከፈለጉ በሚፈልጉት አድራሻ ምዝገባ ማከናወን ናቸው። በዚህም መሰረት እስከ ትላንት ወዲያ ሰኞ ሐምሌ 18፤ 2104 ድረስ፤ 125 ግብር ከፋዮች ለገቢዎች ሚኒስቴር በቀጥታ ማመልከቻ ማስገባታቸውን አቶ ቶሉ ፊጤ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
የታክስ ክሊራንስ ካገኙ 87 አመልካቾች ውስጥ ስልሳ ስድስቱ ለትግራይ ክልል ገቢዎች ቢሮ ግብር ይከፍሉ የነበሩ ግለሰቦች መሆናቸውን የሰሜን ምዕራብ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አስረድተዋል። ቀሪዎቹ 21 ግብር ከፋዮች ደግሞ በገቢዎች ሚኒስቴር መቐለ ቅርንጫፍ ተመዝግበው ግብር ይከፍሉ የነበሩ ድርጅቶች መሆናቸውን አብራርተዋል።
በትግራይ ክልል ተመዝግበው የነበሩት እነዚህ ግብር ከፋዮች የታክስ ክሊራንስ ቢያገኙም ንብረታቸውን መሸጥ እና መለወጥ ግን አይችሉም። በገቢዎች ሚኒስቴር የህግ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አበረ አስፋው ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲያብራሩ “ትግራይ አካባቢ የሚሰሩት ሲመረመር ኃላፊነት ቢኖርባቸው፤ ንብረታቸውን እንዳይሸጡ፣ ጠቅላላ ሀብት እንዳያጠፉ የመንግስት interest ስላለ መሸጥ መለወጥን ሳይጨምር ሌሎች አገልግሎቶች ይሰጧቸው እና ወደ ቢዝነስ ይግቡ ነው የተባለው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታው ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ተፈርሞ ባለፈው ሰኔ ወር መጀመሪያ ለገቢዎች ሚኒስቴር በተላከው ደብዳቤ ላይም ተመሳሳይ ምክንያት ሰፍሯል። በትግራይ ክልል የተመዘገቡ የፌደራል እና የክልል ታክስ ከፋዮች “በክልሉ ካከናወኑት የንግድ ስራ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የሚፈለግባቸው የግብር እና ታክስ ዕዳ መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ ስለማይቻል” ንብረታቸውን መሸጥ እንደማይችሉም ያትታል።
ይኸው የገንዘብ ሚኒስቴር ደብዳቤ፤ ግብር ከፋዮቹ ለትግራይ ክልል እና ለፌደራል መንግስት መክፈል የነበረባቸውን እና ያልከፈሉትን ግብር፤ የገቢዎች ሚኒስቴር እንዲሰበስብ መወሰኑን አመልክቶ ነበር። የገንዘብ ሚኒስቴር ውሳኔ መነሻ እና ዓላማ፤ ግለሰቦች እና ድርጅቶች “ግብር እንዲከፍሉ ብቻ አይደለም” የሚሉት የገቢዎች ሚኒስቴር የሰሜን ምዕራብ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ፤ ይልቁንም ግብር ከፋዮቹ “ወደ ንግድ ስርዓት እንዲገቡ እና ቀጣይ ስራቸውን ማንቀሳቀስ እንዲችሉ” የተላለፈ መሆኑን ያስረዳሉ።
የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የገቢዎች ሚኒስቴር እስካሁን ከክልል እና ከፌደራል ግብር ከፋዮች በድምሩ 15.9 ሚሊዮን ብር ገደማ መሰብሰቡን አቶ ቶሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። የገቢዎች ሚኒስቴር ከሰበሰበው ውዝፍ ግብር ውስጥ 15.4 ሚሊዮን ብር ገደማው የተሰበሰበው ከአራት የፌደራል ግብር ከፋዮች ሲሆን 533 ሺህ ብር ገደማ የሚሆነው ደግሞ ከሰባት የክልል ግብር ከፋዮች ነው።
የሚኒስቴሩ የሰሜን ምዕራብ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት፤ ለትግራይ ክልል ገቢዎች ቢሮ የሚከፍሉ ግለሰብ ግብር ከፋዮችን የግብር ዕዳ የሚሰበስበው ግለሰቦቹ በሚያቀርቡት መረጃ መሆኑን አቶ ቶሉ አስረድተዋል። የግለሰብ ግብር ከፋዮች መረጃ የሚገኘው በትግራይ ክልል ገቢዎች ቢሮ መሆኑን የጠቆሙት ስራ አስኪያጁ፤ “ዕዳ የለብንም” የሚሉ ግብር ከፋዮች ካሉም ክሊራንስ እንደሚያገኙ አብራርተዋል።
ለሁሉም ግብር ከፋዮች በሚሰጠው ጊዜያዊ ክሊራንስ ላይ የዕዳ ማጣራቱ እንደሚቀጥል እና ለአንድ ጊዜ ብቻ እንደሚያገለግል የሚገልጽ ማስታወሻ እንደሚሰፍርበትም ጠቁመዋል። “ለትግራይ ክልል የምንከፍለው ዕዳ አለ ካሉ እሱን ገንዘብ እንቀበላለን። ገንዘቡን ተቀብለን በአደራ የባንክ ሂሳብ እናስቀምጣለን” የሚሉት አቶ ቶሉ ፊጤ፤ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግም በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዝግ የባንክ ሂሳብ መከፈቱን አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)