በሃሚድ አወል
ኢትዮ ቴሌኮም በ2014 በጀት ዓመት 61.3 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ አስታወቁ። ተቋሙ ያገኘው ገቢ በበጀት ዓመቱ በዕቅድ ከያዘው 87.6 በመቶውን ያሳካ እንደሆነም ገልጸዋል።
ፍሬህይወት ይህን የተናገሩት የተቋማቸውን የ2014 በጀት ዓመት የስራ አሰፈጻጸም በተመለከተ በአዲስ አበባው ኢሊሌ ሆቴል እየሰጡት ባለው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ኢትዮ ቴሌኮም ባለፈው ዓመት 56.5 ቢሊዮን ብር ገቢ ያገኘ ሲሆን በ2014 የበጀት ዓመት ደግሞ 70 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ዕቅድ ይዞ ነበር።
ተቋሙ ካለፈው ዓመት የተሻለ ገቢ ያገኘው “ነገሮች አልጋ በአልጋ ስለነበሩ ምቹ ስለነበሩ አይደለም። ብዙ ችግሮች ነበሩ” ሲሉ ፍሬህይወት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መካከል የአገልግሎት መቋረጥ፣ የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ፣ የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የነዳጅ አቅርቦት ማነስ እንዲሁም የጸጥታ ችግር ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
መንግስታዊው የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት በዕቅዱ ያስቀመጠውን ያህል ገቢ ባያገኝም፤ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ግን በተቋማቸው አፈጻጸም ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)