ከኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ላይ ፍርድ ቤት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

በሃሚድ አወል

ከኮንዶሚኒየም ቤቶች ጋር በተያያዘ ከሁለት ሳምንት በፊት በቁጥጥር ስር የዋሉ ስምንት ግለሰቦች ላይ በድጋሚ ለፖሊስ 14 የምርመራ ቀናት ተሰጠ። ለፖሊስ የምርመራ ጊዜውን የሰጠው ዛሬ አርብ ሐምሌ 22፤ 2014 የዋለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።

የምርመራ ጊዜ የተፈቀደባቸው ተጠርጣሪዎቹ የአዲስ አበባ ከተማ የቴክኒክ ሙያ ስልጠና እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ እና የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ሰራተኞች የነበሩ ናቸው። ከተጠርጣሪዎቹ ውስጥ የአዲስ አበባ የቴክኒክ ሙያ ስልጠና እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ምከትል ኃላፊ አቶ አብርሃም ሰርሞሎ ይገኙበታል።  

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በዛሬው ውሎው “ከፖሊስ የምርመራ መዝገብ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ተገንዝበናል” ብሏል። “የወንጀሉ ውስብስብነት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ለመስጠት ምክንያታዊ ነው” ያለው የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ፤ በዚህም መሰረት 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ለመርማሪ ፖሊስ መፈቀዱን አስታውቋል።  

የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ በስምንቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኞች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ቀናትን ሲፈቅድ ይህ ሁለተኛ ጊዜው ነው። ችሎቱ ከ10 ቀናት ገደማ በፊት ሐምሌ 11፤ 2014 በነበረው ውሎው፤ 14 የምርመራ ቀናትን በተመሳሳይ ለፖሊስ ፈቅዶ ነበር። ለፖሊስ የተፈቀዱለት እነዚህ የምርመራ ቀናት፤ ተጠርጣሪዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ችሎት ከቀረቡበት ሐምሌ 8፤ 2014 ጀምሮ የሚታሰብ መሆኑ በወቅቱ መገለጹ ይታወሳል። 

ለሶስተኛ ጊዜ ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት ስምንቱ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉት ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ሐምሌ 6፤ 2014 ነበር። ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ከ10 ቀናት በፊት ሐምሌ 1፤ 2014 በተካሄደው የኮንዶሚኒየም ዕጣ ስነ ስርዓት ላይ “ለዕጣው ብቁ ያልሆኑ ሰዎች እንዲካተቱ አድርገዋል” የሚል ውንጀላ ቀርቦባቸው ነው። “የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ አልተወጡም” በሚል በፖሊስ የተወነጀሉት ግለሰቦች፤ የዋስትና መብታቸው ውድቅ ተደርጎ በእስር ላይ ይገኛሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)