በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩት የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ላይ ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናት ተፈቀደ

በሃሚድ አወል

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ምትኩ ካሳ ላይ በድጋሚ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ። ፍርድ ቤቱ በተመሳሳይ መዝገብ ጉዳዩ እየታየ ባለው ልጃቸው እያሱ ምትኩ ላይም ለፖሊስ 10 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ሰጥቷል። 

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የምርመራ ቀኑን የፈቀደው ኮሚሽነሩ እና ልጃቸው “ከተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት አይነት፣ ውስብስብነት እና ልዩ ባህሪ አንጻር ቢወጡ ምርመራውን ያከብደዋል” በሚል ምክንያት ነው። የፌደራል ፖሊስ አቶ ምትኩን በቁጥጥር ስር ያዋላቸው፤ ኤልሻዳይ ከተሰኘ በጎ አድራጎት ማህበር ባለቤት ጋር በመመሳጠር ለእርዳታ የተዘጋጀን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶችን “ለግል ጥቅም አውለዋል” በሚል በሙስና ወንጀል በመጠርጠሩ መሆኑን አስታውቆ ነበር።

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነሩ ከዚህ በተጨማሪም “ሕገወጥ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ወንጀል” መጠርጠራቸውን የፌደራል ፖሊስ መግለጹ ይታወሳል። ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ ምትኩ ካሳ እና ልጃቸው እያሱ ምትኩ፤ ተጨማሪ የምርመራ ቀናትን በተመለከተ በመርማሪ ፖሊስ እና በጠበቆቻቸው እና መካከል የተደረገውን ክርክር በአካል ተገኝተው ተከታትለዋል።

የፌደራል ፖሊስ በዛሬው የችሎት ውሎ፤ ባለፈው ቀጠሮ በተፈቀዱለት 14 የምርመራ ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። ባለፉት 14 ቀናት “በርካታ ስራዎችን ሰርተናል” ያሉት የፌደራል ፖሊስ መርማሪዎች፤ የ12 ምስክሮችን ቃል መቀበላቸውን ገልጸዋል። ከወንጀሉ ጋር የተያያዙ ማስረጃዎችን ለማግኘትም ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት አለው ለተባለው ኤልሻዳይ በጎ አድራጎት ማህበርን ጨምሮ ለተለያዩ ተቋማት ደብዳቤ ደብዳቤ መጻፋቸውንም አክለዋል። 

የፌደራል ፖሊስ ማስረጃ ለማሰባሰብ ደብዳቤ ከጻፈላቸው ተቋማት ውስጥ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን፣ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እና የተለያዩ ባንኮች ይገኙበታል። ፖሊስ ለእነዚህ ተቋማት ለጻፋቸው ደብዳቤዎች ምላሽ ለመቀበል እና ስለ ወንጀሉ ያስረዳሉ የተባሉ ቀሪ 15 ምስክሮችን ቃል ለመቀበል፤ ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ለፍርድ ቤት ጥያቄውን አቅርቧል።  

ተጠርጣሪዎቹን ወክለው በችሎት የተገኙት ሁለት ጠበቆች በበኩላቸው፤ ፖሊስ ለጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ያቀረባቸው ምክንያቶች ዋስትና ስለማያስከለክሉ ደንበኞቻቸው የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል። ከጠበቆቹ መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሀብተማሪያም ጸጋዬ አንደኛ ተጠርጣሪ አቶ ምትኩ ካሳን በተመለከተ ባቀረቡት መከራከሪያ፤ “ወጪ የተደረገውን  እርዳታ በተገቢው መንገድ መዋሉን የመከታተል ስልጣን፤ ተጠርጣሪው የሚመሩት ተቋም ኃላፊነት አይደለም” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

ድጋፍ እናደርጋለን የሚሉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ከመንግስት ጋር “operational agreement” እንደሚፈራረሙ የጠቆሙት ጠበቃው፤ ይህን ስምምነት የመከታተል ኃላፊነት የሚወድቀውም በክልል አደጋ ስጋት ቢሮዎች እና የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መሆኑን ጠቅሰዋል። ደንበኛቸው “የተረጂዎችን ቁጥር የማሳነስም የመጨመርም ስልጣን ያላቸው አይደሉም” ያሉት አቶ ሀብተማሪያም፤ አቶ ምትኩ በኃላፊነታቸው ምክንያት መፈረም ያሉባቸው ጉዳዮች ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸውን ተናግረዋል። “ያ ፊርማ እየተለቀመ የተሰራው ሁሉ ወንጀል ነው ማለት አግባብ የለውም” ሲሉም ተከራክረዋል። 

ፖሊስ አቶ ምትኩ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ቀን ይፋ ባደረገው መረጃ፤ በሌሉ ተረጂዎች ስም እና የተረጂዎችን ቁጥር በማጋነን 472 ሚሊዮን ብር ለኤልሻዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት ተሰጥቷል ሲል ወንጅሎ ነበር። ኮሚሽነሩ ከዚህ በተጨማሪም ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚገመት 512 ሺህ ኩንታል ስንዴ እንዲሁም ሌሎች ምግብ ነክ ቁሳቁሶች ከተራድኦ ድርጅቱ ጋር በመመሳጠር ለግል ጥቅም መዋላቸውን ፖሊስ ማስታወቁ ይታወሳል።

እጃቸው እስከተያዘበት ጊዜ ድረስ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንን በኮሚሽነርነት ሲመሩ የነበሩት አቶ ምትኩ ካሳ፤ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ሐምሌ 6፤ 2014 ነበር። በግብርና ሚኒስቴር የአደጋ ስጋት አመራር እና የምግብ ዋስትና ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ለስምንት ዓመታት ያገለገሉት አቶ ምትኩ፤ ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት በ2008 ዓ.ም ነበር።

በዛሬው ችሎት የኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ልጅ የሆነው ሁለተኛ ተጠርጣሪንም በተመለከተ ጠበቆች መከራከሪያ አቅርበዋል። ሁለተኛ ተጠርጣሪ አቶ እያሱ ምትኩን በተመለከተ ፖሊስ “ሰርቼያችኋለሁ” ብሎ የገለጸው አሊያም “በቀጣይ እንሰራዋለን ተብሎ የተለየ ነገር የለም” ያሉት ጠበቃ ፈቲ ኑሬ፤ ደንበኛቸው አላግባብ መታሰራቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል።

አቶ ፈቲ ደንበኛቸው፤ “የአንደኛ ተጠርጣሪ ልጅ በመሆናቸው እና በደፈናው አንደኛ ተጠርጣሪ በእሳቸው ስም መኪና እንዲገዛ አድርገዋል በሚል ተራ ጥርጣሬ” መታሰራቸውን አክለዋል። መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ፤ ሁለተኛ ተጠርጣሪው አቶ እያሱ ምትኩ “በህገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ በመገልገል” እንደጠረጠራቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። 

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤቱ፤ በሁለተኛ ተጠርጣሪ ስም መኪና መገዛቱ በፖሊስ በማስረጃ መቅረቡን አስታውሶ፤ “ይህ እሱ በማያውቀው ሁኔታ [የተደረገ] ነው ለማለት አያስችልም” ብሏል። ችሎቱ አክሎም ተጠርጣሪው ከሙስና ወንጀሉ ጋር በተያያዘ ሳይሆን “በህገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ በመገልገል” መጠርጠራቸውን በመጥቀስ ፖሊስ ለችሎት ያቀረበውን ገለጻ አረጋግጧል።

በዛሬው ችሎት በተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች የተነሳውን የዋስትና ጥያቄም መርማሪ ፖሊስ ተቃውሞታል። ፖሊስ ማስረጃዎችን የሚሰበስበው ተጠርጣሪው ይመሩት ከነበረው መስሪያ ቤት እና ከክልል ቢሮዎች ስለሆነ፤ ተጠርጣሪው ቢወጡ ማስረጃዎችን ለማምጣት እንደሚቸገር ገልጿል። 

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጠበቆች በኩል የቀረበውን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ቀናትን  ፈቅዷል። የአቶ ምትኩን ጉዳይ ለመመልከት ለነሐሴ 6፤ 2014 ቀጠሮ የሰጠው ፍርድ ቤቱ፤ የሁለተኛው ተጠርጣሪ ጉዳይ ለመመልከት ደግሞ ለነሐሴ 2 በመቅጠር የዛሬ ውሎውን አጠናቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)