በቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ላይ ፍርድ ቤት ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናት ፈቀደ

በሃሚድ አወል

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት “በስልጣን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል” በተጠረጠሩት የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉቀን ሀብቱ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ 14 የምርመራ ቀናትን ፈቀደ። ፍርድ ቤቱ የምርመራ ጊዜውን የፈቀደው “ከወንጀሉ ልዩ ባህሪ እና ውስብስብነት አንጻር ምርመራው በአጭር ጊዜ የሚቋጭ አይደለም” በሚል ምክንያት ነው።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 25፤ 2014 በነበረው ውሎ፤ የፖሊስን የተጨማሪ ምርመራ ቀናት ይፈቀድልኝ ጥያቄ እና የተጠርጣሪው ጠበቃ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ አድምጧል። በዛሬው የችሎት ውሎ ለፖሊስ ከሁለት ሳምንት በፊት በተፈቀዱለት 14 ቀናት ተከናውነዋል የተባሉ ተግባራትም በዝርዝር ቀርበዋል።

መርማሪ ፖሊስ በእነዚህ ቀናት የተጠርጣሪውን የጣት አሻራ መውሰዱን እና ተጠርጣሪውን ማነጋገሩን ገልጿል። ከኮንዶሚኒየም ዕጣ አወጣጥ ጋር በተያያዘ ኦዲት ሪፖርት ተሰርቶ እንዲላክለት የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎትን (INSA) በደብዳቤ መጠየቁን ፖሊስ ለችሎቱ ተናግሯል። ዕጣው የወጣባቸውን እና ሲስተሙ የተጫነባቸውን “ላፕቶፕ ኮምፒዩተሮች” ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተረክቦ ለINSA መላኩንም አክሏል።

የተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት ላይ ብርበራ ማድረጉን የገለጸው ፖሊስ፤ በብርበራው የሳተላይት ስልክ እና ጦር መሳሪያ ተገኝቷል ብሏል። ዝርዝር የሀብት ጥናት ለማድረግ “ለሚመለከተው አካል” ጥያቄ ማቅረቡንም ፖሊስ ጠቁሟል። “ወንጀሉ ከተለያዩ ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር የተፈጸመ ነው” ያለው መርማሪ ፖሊስ፤ ቀሪ ስራዎችን ለማከናወን 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲፈቅድለት ችሎቱን ጠይቋል።  

ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ቀናትን የጠየቀው የምስክሮችን ቃል ለመቀበል እንዲሁም ከINSA የኦዲት ሪፖርት ለማምጣት በሚል ነው። “አላግባብ [በኮንዶሚኒየም] ዕጣው የተካተቱ ሰዎችን በመለየት ከተጠርጣሪዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጣራት” የሚለውም ለምርመራ ቀናት መጠየቂያ በምክንያትነት ቀርቧል።

ዶ/ር ሙሉቀንን ወክለው በችሎት የተገኙት ጠበቃቸው አቶ ሞላልኝ መለሰ፤ ፖሊስ ቀሩኝ ያላቸው ስራዎች “የተጠርጣሪውን በማረፊያ ቤት መቆየት አይፈልጉም” ሲሉ ተከራክረዋል። የእጣ አወጣጡን ሂደት ኦዲት መደረግ በተመለከተም ተጠርጣሪው በተገኙበት ኦዲት መደረግ እንዳለበት ገልጸዋል። ዶ/ር ሙሉቀን የፖለቲካ ተሿሚ መሆናቸው ያነሱት አቶ ሞላልኝ፤ “ዝርዝር ቴክኒካል ስራዎች ላይ መሳተፍ” የደንበኛቸው ኃላፊነት አለመሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል።

“የሀብት ምርመራ በማን ላይ እየተከናወነ መሆኑ አልተገለጸም” ያሉት አቶ ሞላልኝ፤ ፖሊስ በቀጥታ ከተጠርጣሪው ጋር በተያያዘ ያከናወናቸውን ተግባራት እና ቀሪ ስራዎችን አላቀረበም ሲሉ ተሟግተዋል። ዶ/ር ሙሉቀን የተጠረጠሩበት ወንጀል ዋስትና የማያስከለክል መሆኑን እና ዋስ እንዲያቀርቡ ቢጠየቁ ማቅረብ እንደሚችሉ በማንሳት፤ የደንበኛቸው የዋስትና መብት እንዲከበር ጠበቃው ችሎቱን ጠይቀዋል። 

በችሎቱ ዕድል ተሰጥቷቸው የተናገሩት ዶ/ር ሙሉቀን፤ በቤታቸው የተገኙት የሳተላይት ስልክ እና የጦር መሳሪያ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ስራ አስፈጻሚ በነበሩበት ወቅት የተሰጧቸው መሆኑን ገልጸዋል። በተጠረጠሩበት ወንጀል ላይ ተሳትፎ እንደሌላቸው የገለጹት የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቢሮ ኃላፊ፤ “እኔን [በእስር] ለማቆየት የሚደረግ እንጂ እኔ በቀጥታ ተሳትፎ ያደረግኩበት አይደለም” ብለዋል። ዶ/ር ሙሉቀን የቤተሰብ ኃላፊ መሆናቸውን በመግለጽ ጠበቃቸው ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ በድጋሜ ለችሎቱ አቅርበዋል።

ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ችሎት ፊት የቀረቡት ዶ/ር ሙሉቀን በቁጥጥር ስር የዋሉት “በስልጣን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል” ተጠርጥረው ነው። ዶ/ር ሙሉቀንን ለእስር ያበቃቸው ሐምሌ 1፤ 2014 በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወጣው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ ጋር በተያያዘ ተፈጽሟል የተባለው የማጭበርበር ወንጀል ነው።

በከንቲባ አዳነች አቤቤ የሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ አባል የነበሩት ዶ/ር ሙሉቀን፤ የአዲስ አበባ ቴክኒክ ሙያ ስልጠና እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮን ላለፉት ዘጠኝ ወራት በኃላፊነት ሲመሩ የነበሩ ናቸው። ዶ/ር ሙሉቀን የከንቲባ አዳነች አቤቤን ካቢኔን ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀላቀሉት በጥቅምት 2013 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሲሾሙ ነበር።  

ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ያለመከሰስ መብታቸው በአዲስ አበባ ምክር ቤት ተነስቶ ሐምሌ 8፤ 2014 በቁጥጥር ስር የዋሉት ዶ/ር ሙሉቀን፤ በችሎት በንግግራቸው መሐል ስሜታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ሲያለቅሱ ተስተውለዋል። ይህን የተመለከቱት የመሀል ዳኛውም ዶ/ር ሙሉቀን ጉዳያቸውን ተቀምጠው እንዲከታተሉ አድርገዋል።

ተጠርጣሪው እና ጠበቃቸው በዛሬው ችሎት ያነሱት የዋስትና ጥያቄ በመርማሪ ፖሊስ ተቃውሞ ቀርቦበታል። “ከኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ከዋሉ ተጠርጣሪዎች ትልቁ እሳቸው ናቸው” ያለው ፖሊስ፤ “የእርሳቸው መፈታት ምስክር እንዳይመጣ ያደርጋል” ሲል ተቃውሞን አሰምቷል።   

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ችሎቱ ከፖሊስ የምርመራ መዝገብ “ምርመራው ሰፊ መሆኑን መገንዘቡን” እና “በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን” ገልጿል። ስለሆነም “ለምርመራው ውጤታማነት ሲባል” ተጠርጣሪው ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለፖሊስ 14 የምርመራ ቀናትን ሰጥቷል።

የችሎት ውሎው ከመጠናቀቁ በፊት ዶ/ር ሙሉቀን በቁጥጥር ስር ከዋሉበት ቀን ጀምሮ ቃል አለመስጠታቸውን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ የምርመራ ሂደቱ ላይ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል። መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ የተጠርጣሪውን ቃል ያልተቀበለው፤ ከINSA ይመጣል የተባለውን ሪፖርት እየተጠባበቀ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለነሐሴ 9፤ 2014 በሰጠው ቀጣይ ቀጠሮ፤ ፖሊስ ከተጠርጣሪው ጋር ብቻ በተያያዘ የተሰሩ ስራዎች እና በቀጥታ የተሳትፏቸውን መጠን ለብቻ ተለይቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ አስተላልፏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)