በደቡብ ክልል ያሉ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች በሁለት የተለያዩ ክልሎች ለመደራጀት በምክር ቤቶቻቸው ውሳኔዎችን አሳለፉ

በደቡብ ክልል የሚገኙ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች በሁለት የተለያዩ ክልሎች አንድ ላይ ለመደራጀት በምክር ቤቶቻቸው ውሳኔዎችን አሳለፉ። የወላይታ፣ ጌዲኦ፣ ጋሞ፣ የደቡብ ኦሞ እና ኮንሶ ዞኖች በአዲስ የሚደራጀውን ክልል ለመቀላቀል ዛሬ ቅዳሜ ሐምሌ 23፤ 2014 ባካሄዱት ጉባኤ ወስነዋል። 

የአማሮ፣ ባስኬቶ እና አሌ ልዩ ወረዳዎችም በምክር ቤቶቻቸው ተመሳሳይ ውሳኔ አጽድቀዋል። ጉባኤውን እያካሄደ የሚካሄደው የቡርጂ ልዩ ወረዳ አዲሱን የክልል አደረጃጀት የሚያጸድቅ ከሆነ በስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች የሚደራጀውን አዲስ ክልል ይቀላቀላል። 

በሌላ በኩል የሀድያ፣ ሀላባ እና ከምባታ ጠምባሮ ዞኖች እንዲሁም የየም ልዩ ወረዳ ምክር ቤት ከሌሎች ሁለት ዞኖች ጋር በመሆን አንድ የጋራ ክልል ለመመስረት ወስነዋል። ቀሪዎቹ ሁለት ዞኖች የጉራጌ፣ እና ስልጤ ዞኖች የክልል አደረጃጀቱን ገና በምክር ቤቶቻቸው አላጸደቁም።  

በደቡብ ክልል ያሉት አስራ አንዱም ዞኖች እና ስድስት ልዩ ወረዳዎች ምክር ቤቶች ተመሳሳይ ውሳኔዎችን የሚያሳልፉ ከሆነ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በሁለት ይከፈላል። ከዚህ በፊት በደቡብ ክልል ስር ተደራጅተው የነበሩት የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በህዝበ ውሳኔ የራሳቸውን ክልል መስረተው ከክልሉ መውጣታቸው ይታወሳል። (በሃሚድ አወል – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)