ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል “የደህንነት ዋስትና” የሚሰጥ ደብዳቤ ለፌደራል መንግስት ላኩ

የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በትግራይ የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማስጀመር ወደ ክልሉ ማቅናት ለሚፈልጉ አካላት የደህንነት ዋስትና የሚሰጥ ደብዳቤ ለፌደራል መንግስት ላኩ። ዶ/ር ደብረጽዮን ደብዳቤውን ለዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ማስረከባቸውን የአውሮፓ ህብረት አስታውቋል።

የአውሮፓ ህብረት ይህን ያስታወቀው የህብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አኔት ዌበር እና የአሜሪካ አቻቸው ማይክ ሐመር የተካተቱበት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስብስብ ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 26፤ 2014 ወደ መቐለ ተጉዘው ከትግራይ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ከተወያዩ በኋላ ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ሃና ቴትን ጨምሮ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የካናዳ እና ጣሊያን አምባሳደሮች እንዲሁም የአሜሪካ “ቻርዥ ደ አፌር” የዛሬው ጉዞ አካል ነበሩ።

የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አኔት ዌበር እና የአሜሪካ አቻቸው ማይክ ሐመር የተካተቱበት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስብስብ ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 26 ወደ መቐለ ተጉዞ ውይይት አድርጓል | ፎቶ፦ ድምፂ ወያነ

ለመጀመሪያ ጊዜ በጥምረት ወደ መቐለ የተጓዙት የአውሮፓ ህብረት እና የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑካን፤ የኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮም እና ባንክን ጨምሮ በትግራይ ክልል የተቋረጡ ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ መጀመር እንደሚኖርባቸው መስማማታቸውን መግለጫው ጠቁሟል። በትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት የደህንነት ማረጋገጫ በመቅረቡ ከዚህ በኋላ “[መሰረታዊ] አገልግሎቶችን ለማስጀመር ምንም መሰናክል ሊኖር አይገባም” ሲል የአውሮፓ ህብረት በመግለጫው አሳስቧል።

ዛሬ ወደ መቐለ የተጓዙት ልዩ ልዑካን፤  በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የሰላም ድርድር እንዲጀመር የማበረታታት ዓላማ አንግበው መሆኑን የአውሮፓ ህብረት መግለጫ አመልክቷል። ሁለቱ ዲፕሎማቶች ወደ ትግራይ ከማቅናታቸው በፊት ባለፈው ሳምንት ከፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ እና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በአዲስ አበባ ተገናኝተው መወያየታቸው ይታወሳል። 

አኔት ዌበር እና ማይክ ሐመር፤ በግጭቱ የሚሳተፉ ሁሉም ወገኖች “ከጥላቻ ንግግር እና ጠብ ጫሪ መግለጫዎች” እንዲቆጠቡ ጥሪ ማስተላለፋቸውን የአውሮፓ ህብረት መግለጫ ጠቁሟል። ሁለቱ ልዩ ልዑካን፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመመርመር ያቋቋመው ኮሚሽን አባላት ተዓማኒ ምርመራ ማከናወን ይችሉ ዘንድ፤  ግጭት የነበረባቸውን አካባቢዎች መጎብኘት እንዲችሉ ትብብር እንዲደረግላቸው ማበረታታቸውንም መግለጫው አመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)