የደቡብ ክልል ለአዲሱ የስርዓት ትምህርት የሚያስፈልጉ መጽሐፍትን ለማሳተም 4.6 ቢሊዮን ብር ያስፈልገኛል አለ

በሃሚድ አወል

የደቡብ ክልል በ2015 የትምህርት ዘመን ተግባራዊ ለሚያደርገው አዲሱ የስርዓት ትምህርት የሚያስፈልጉ መጽሃፍትን ለማሳተም 4.6 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው ገለጸ። ክልሉ አዲሱን ስርዓተ ትምህርት ተከትለው የተዘጋጁ፤ ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች መማሪያ እና የመምህራን መርጃ የሚሆኑ 26 ሚሊዮን መጽሐፍትን ለማሳተም ማቀዱን የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቋል። 

የትምህርት ቢሮው ለመጽሐፍት ማሳተሚያ ያስፈልገኛል ያለው የገንዘብ መጠን፤ የደቡብ ክልል ለ2015 በጀት ዓመት ለክልላዊ ፕሮግራሞች፣ ተቋማት እና ሴክተር መስሪያ ቤቶች በያዘው 8.8 ቢሊዮን ብር ይሸፈን ቢባል ግማሽ ገደማውን ይይዛል። የደቡብ ክልል ምክር ቤት ለ2015 በጀት ዓመት 46.3 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ የገንዘብ መጠን ከሳምንት በፊት ማጽደቁ ይታወሳል። 

የደቡብ ክልል አዲሱን ስርዓት ትምህርት በ100 ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ማደረግ የጀመረው በ2014 የትምህርት ዘመን ነው። ክልሉ በቀጣዩ ዓመት፤ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል በሚያስተምሩ ሁሉም ትምህርት ቤቶች አዲሱን የስርዓተ ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ ማቀዱን የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ስምዖን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

በትምህርት ቢሮው የስርዓት ትምህርት ዝግጅት ትግበራ እና የቴክኖሎጂ አቅርቦት ዘርፍን በኃላፊነት የሚመሩት አቶ ስንታየሁ፤ አዲሱን ስርዓተ ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ በክልሉ ላሉ ትምህርት ቤቶች የሚሰራጩ 26 ሚሊዮን መጽሐፍት እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል። እነዚህን መጽሐፍት ለማሳተም “በጣም ብዙ ገንዘብ ይጠይቃል” የሚሉት ምክትል የቢሮ ኃላፊው፤ አሁን ባለው የገበያ ዋጋ መሰረት ክልሉ ለመጽሐፍት ህትመት ብቻ 4.6 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው መገመቱን አስረድተዋል። 

ለመጽሐፍት ህትመት የሚፈለገውን ከፍተኛ ገንዘብ የክልሉ “መንግስት ብቻውን የሚችለው አይደለም” ያሉት አቶ ስንታየሁ፤ ክልሉ አማራጭ የገንዘብ ምንጮችን ለመጠቀም እንዳሰበ ጠቁመዋል። “ህብረተሰቡን በማሳተፍ እንዲሁም፤ የወረዳ እና ዞን መንግስታት በጋራ በመሆን መምራት የሚያስችል ሁኔታ እንፈጥራለን” ሲሉ ክልሉ ተግባራዊ ለማድረግ ያቀደውን የገንዘብ ማፈላለጊያ መንገድ አመልክተዋል።   

ከመጽሐፍት ህትመት ወጪ ጋር በተያያዘ የክልሉ መንግስት የገጠመውን ተግዳሮት ለመቅረፍ በአማራጭነት የያዘው ሌላው ጉዳይ በ“ሶፍት ኮፒዎች” ለትምህርት ቤቶች እንዲዳረሱ ማድረግን ነው። አቶ ስንታየሁ “ደረጃውን የጠበቀ መጽሐፍ ባናዘጋጅም፤ ገጠርም ከተማም ላሉ ትምህርት ቤቶች በሶፍት ኮፒ በኮምፒውተሮች በማዳረስ፤ አሁን ባለው እንጀምር ብለን ነው” ሲሉ የክልሉ ትምህርት ቢሮ መጪውን የትምህርት ዘመን በምን መልኩ ለመቀበል እንዳቀደ አብራርተዋል። 

የደቡብ ክልል በ2014 አዲሱን ስርዓተ ትምህርት በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ባደረገባቸው 100 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተመሳሳይ የመጽሐፍት እጥረት ችግር አጋጥሞት እንደነበር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ከሳምንት በፊት ባቀረቡት የበጀት ዓመት ማጠቃለያ ሪፖርት ገልጸው ነበር። በአዲሱ የስርዓተ ትምህርት ማዕቀፍ መሰረት የሚታተሙ መጽሐፍት እስኪደርሱ ድረስ፤ ቀደም ብለው የተዘጋጁ የመማሪያና ማስተማሪያ መጻሐፍት “እስከ ምዕራፍ ሶስት ያለውን” ኮፒ በማድረግ በዞንና ልዩ ወረዳዎች አማካኝነት ለተማሪዎች መሰራጨቱን አቶ እርስቱ በሪፖርታቸው አስታውቀዋል።  

በ2014 በጀት ዓመት ክልሉ “ለአንድ ተማሪ አንድ መጽሐፍ” ለማዳረስ በያዘው እቅድ 839,085 ኮፒ አሳትሞ ለዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ማከፋፈሉን ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው ላይ አመልክተዋል። የደቡብ ክልል የእነዚህን መጽሐፍት ህትመት እና ግዢ ያከናወነው ከመንግስታዊው የትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት መሆኑን የጠቀሱት አቶ እርስቱ፤ ለዚህም ክልሉ 135 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን በሪፖርታቸው አስታውቀው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)